top of page

ጸሎት አስተምረን--የኃጢያት ይቅርታ (ክፍል አስራ-ሁለት)

እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ...

እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር

አባታችን ሆይ

...

ኃጢአታችንንም ይቅር በለን

...” (ሉቃ. 11፡3)

በአባታችን ሆይ ጸሎት ውስጥ ሌላው የምንጸልየው ሃሳብ ስለ ኃጢያት ይቅርታ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ስለነበርንበት ሁኔታ ሲያነሳ በኃጢያታችንና በበደላችን ሞታን

እንደነበርን ይናገራል። (ኤፌ. 2፡1) የምንመላለሰው የዲያቢሎስን ፍቃድ በማድረግ ነበር።

የስጋችንንም ምኞት እየፈጸምን እንኖር ነበር። ከፍጥረታችንም ለእግዚአብሔር ቁጣ የተጠበቅን

የቁጣ ልጆች ነበርን። አሁን ግን ሙታን ለነበርነው የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሕይወት

ተሰጥቶናል። ከኃጢያት ባርነት ወጥተን ለእግዚአብሔር ፍቃድ የምኖርበትን የጸጋ አቅም

አግኝተናል። ከቁጣ ልጅነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት መጥተናል። ይህ ሁሉ የሆነልን

ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅርና ምህረት የተነሳ ነው። እኛ ይቅር የተባልን፣ በምሕረት ኩነኔ

የቀረልን ሰዎች ነን። እንግዲህ በእግዚአብሔር ጸጋ የማይገባንን የኃጢያት ይቅርታ አግኝተናል።

እለት እለት ስንኖር ደግሞ ለመተላለፋችን የሚሆን የኃጢያት ይቅርታ ከእግዚአብሔር

ዘንድ እንቀበላለን። በ1ኛ ዮሐንስ ላይ እንደምናነበው ኃጢያታችንን ብንናዘዝ እግዚአብሔር

“ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” (1፡9) የጌታ የኢየሱስ

ክርስቶስ ደም አንጽቶ ቀድሶናል። አሁንም ደግሞ በክርስትና ህይወት ስንመላለስ ለመተላለፋችን

መንጻት የክርስቶስ ኢየሱስ ደም አለን። ክርስቲያን በሐጢያት ጸንቶ ሊኖር አይችልም ነገር ግን

በክርስትና ሕይወት መተላለፍ ሊኖር ይችላል። ድካም ሊኖር ይችላል። ያን ጊዜ ስለ ኃጢያት

ይቅርታ መጸለይ አስፈላጊ ነው። መንፈስ ቅዱስ በሚያመለክተን ድካማችን ሁሉ ላይ ድምጹን

እየሰማን በንስሃ መቅረብ ትክክለኛ የክርስትና አቋም ነው። ድካምን መካድ መፍተሄ አይሆንም

ነገር ግን በድካማችን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ መታደስንና ጸጋን እንድናገኝ ያደርገናል። ኢየሱስ

ክርስቶስ ስለኛ ድካም የሚራራ ሊቀ ካህናችን ነው። “ጌታ ሆይ ይህንን መተላለፌን፣ ይህንን

ድካሜን ይቅር በለኝ” ስንለው ስለኛ ሆኖ እንደ ታረደ በግ ከሚታየው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ

የተነሳ እግዚአብሔር ይቅር ይለናል። ምህረትን ያደርግልናል።

ወገኖቼ፦ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ዳግም እድልን የሚሰጥ አምላክ ነው። ልጆቹን እስከ

መጨረሻው ወዷል። የጠፋው ልጅ ወደ ቤት በተመለሰ ጊዜ አባቱ ከሩቅ አይቶት ወደ እርሱ ሮጦ

አቀፈው፤ ልብሱ እንዲለወጥለት አደረገ፤ ቀለበት አደረገለት። ድግስ፣ ምስጋናና ደስታ ሆነ።

እምላካችን የምህረት አምላክ ነው! በልጆቹ ንስሃና መመለስ ደስ ይለዋል። እናስታውስ

የእግዚአብሔር ዙፋን የጸጋና የምሕረት ዙፋን ነው። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page