top of page

የሚያሳጣን የለም!

አንድ ጊዜ ቆንጮ ቱጃሩ ጆን ዲ ሮክፌለር “ለአንድ ሰው ምን ያህል ገንዘብ ይበቃዋል -- how much money is enough” ተብለው ተጠይቀው ነበር። እሳቸውም “ባለህ ላይ ጥቂት ሲጨማር ብለው መለሱ -- just a little bit more” በማለት መለሱ። የቱጃሩ መልስ የሰው የፍላጎት ቋት ማብቂያ የሌለው እንደሆነ የሚገልጽ ነው። እርግጥ ነው የሰው ልጅ ፍላጎት ተጓዥ ኢላማ ነው -- ደረስኩበት ስንለው ይሸሻል -- አንዱን ያዝኩት ስንል ሌላው ያምረናል። ሰው በገንዘቡ ብዛት አይረካም። ዝናም አያጠግብም። ስልጣንም እንደ ጨው ውሃ ነው -- ሲጠጡት እየጨመረ ይጠማል።

መዝሙረኛው ዳዊት ግን አስደናቂ ቅኔን ተቀኘ። እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣ የሚያሳጣኝ የለም አለ። (መዝ፡23) ንጉስ ዳዊት የሚለን እግዚአብሔር ካለኝ ሙሉ ነኝ። እግዚብሔር ካለኝ ጠግቤ አድራለሁ ነው። በእርግጥም የሰው የነብስ ጥማት ሊሞላ የሚችለው በእግዚአብሔር ብቻ ነው። የማረፋችን ምክንያት እግዚአብሔር ለያንዳንዳችን እረኛችን ሰለሆነ ነው። ማረፍ የሚቻለው በእግዚአብሔር ማንነት ላይ ነው። እርሱ ማልካም፣ የሚራራና ብርቱ እረኛ ነው። እርሱ የሚመግብ፣ የሚጠብቅና ዋስትና የሚሆን እረኛ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ መልካም እረኛ ነኝ አለ። መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለበጎቹ ያኖራል። (ዬሐ 10፡ 11) እርሱ “በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ” ነው። (ዕብ 13፡20)

ወገኖቼ፦እርሱ የነብሳችን እረኛና ጠባቂ ነው። (1ጴጥ 2፡25) እረኛችን እግራችንን ለመናወጥ አይሰጠውም። የሚጠብቀን አይተኛም፣ አያንቀላፋምም። (መዝ 121፡3-4) እርሱ የነብሳችን እንጀራ፣ የሕይወት ውሃችን ነው። እርሱ እርካታችን ነው። ነብሳችንን ስለስሙ በጽድቅ መንገድ ይመራል። የራሳችን ጽድቅ የለንም። ስለ ስሙ ሲል (እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ) የራሱን ጽድቅ አለበሰን። ሁል ጊዜ ነብሳችንን በቃሉና በመንፈሱ ይመልሳል። በርሱ ላይ የሚተማመኑትን ሃይላቸውን ያድሳል። ከክፉ መጠበቂያና ማምለጫችን እርሱ ነው። ከርሱ የተነሳ ሞት መውጊያው ተነጥቋል። ሲዖል ድል መንሳት የለውም።

ወገኖቼ፦ ክርስትና የሚጀምረው ከማረፍ ነው። ቃሉ እረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ ይለናል። (መዝ 46፡10) አምላካችን የሚያሳርፍ አምላክ ነው። የተጠራነው የኛን ከባድ የድካም፣ የሃጢያትና የጭንቀት ሸክም አራግፈን የእርሱን ቀሊል ቀንበር እንድሸከም ነው። ቃሉም ሲመክረን “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ይለናል። (ማቴ 11፡28-30) በርሱ ላይ ሆነን ሸክምን መሸከም አይገባንም፤ ደግሞም የለብንም። እምነትና ጭንቀት ተጓዳኝ አይደሉም። ጌታ በአንዳች ነገር አትጨነቁ ይለናል። የሰማይና ይምድር ጌታ እርሱ አባታችን ነው። እርሱ የሚያሳጣን የለም።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page