top of page

መንፈስ ቅዱስ ከኛ ጋር፤ መንፈስ ቅዱስ በኛ ውስጥ።

“እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል ... ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐ. 14፡ 15-17)

መንንፈስ ቅዱስ በአንድ ጊዜ ሁሉም ስፍራ የሚገኝ (“omnipresent”) አምላክ ነው። በመሆኑም ቃሉ እንደሚያስተምረን መንፈስ ቅዱስ አብሮን ያለ ብቻ ያለ ሳይሆን በውስጣችንም ይኖራል። ይህ አስደናቂ እውነት ነው። አለምን የፈጠረ አምላክ (መንፈስ ቅዱስ) ሁልጊዜ በውስጣችን አለ። በዚያው ቅጽበት በአለም ሁሉ ነው። ለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ በውስጣችን ያለውን ጌታ መንፈስ ቅዱስ በጉባኤችንም እንዲመጣ የምንጸልየው።

ይህ “እግዚአብሔር ከኛ ጋር” መሆኑ የአዲስ ኪዳን ልምምድ ነው። በብልይ ኪዳን ግን እንደዚህ አልነበረም። በቡሉይ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ በተለዩ ሰዎች ላይ መጥቶ ኃይል ይሰጣቸውና የእግዚአብሔርን ኃሳብ እንዲያገልገሉ/እንዲፈጽሙ ይረዳቸው ነበር። ለምሳሌ እግዚአብሔር መንፈሱን በሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ላይ ባደረገ ጊዜ ሰባዎቹ ትንቢት ተናገሩ፤ ካዛ በኋላ ግን አልተናገሩም (ዘሑ 11፡25)። ሳምሶንንም “የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ” ያነቃቃው ነበር። (መሳ 13፡25)። በሳኦል ላይ መንፈስ ቅዱስ በመጣበት ጊዜ ከነበያት ጉባዔ ጋር ተቀላቅሎ ትንቢት እንደተናገረ እናነባለን።

በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ ከኛ ጋራና በኛ ውስጥ ነው። ይህ ነብያት አስቀድመው የተነበዩት እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን በኩል የፈጸመው የአዲስ ኪዳን እውነታ ነው። በሕዝቅኤል 36፡ 27 ላይ ቃሉ “መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ” በማለት ይህንን እውነት ከብዙ ዘመን በፊት አረጋግጦልናል። እንዲሁም በሕዝቅኤል 37፤14 ላይ “መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ” ይለናል። በኛ ውስጥ ያለውንና ከኛ ጋር ያለውን ቅዱሱን መንፈስ የምናውቀው ጌታን አንዳኛችን አድርገን የተቀበልን ብቻ ነን። አለም ግን ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እኛ ግን ህልውናውን፣ ማጽናናቱን፣ አብሮነቱን፣ አጋዥነቱን፣ ሃይሉን፣ ፍቅሩንና ምሪቱን እንረዳለን።

ወገኖቼ፤ እኛ የግዚአብሔር መንፈስ የሚኖርብን የርሱ ቤተ መቅደሶች ነን። ሓዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲያስተምረን “ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?” (1ቆሮ 6፡19) በማለት ይጠይቀናል። ስለሆነም ሁልጊዜ ክብሩን ይዘን የምንቀሳቀስ እንደሆንን ልናስተውል ይገባናል። ይህንን እውነት ስንረዳም የምንፈሱ ማደሪያ የሆነውን መቅደስ እንዴት በቅድስና መጠበቅ እንዳለብን እንገነዘባለን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page