top of page

ትንሳኤና ሕይወት ክርስቶስ ነው።

“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል።” (ዮሐ. 11:25)

ትንሳኤ ድል ነው። ትንሳኤ ዳቢሎስ የተዋረደበት ድል ነው። ትንሳኤ የሞትና የሲኦል ሃይል ተሽሮ ሕይወት የነገሰበት ድል ነው። ትንሳኤ ጨላማ በብረሃን የተሻረበት ድል ነው። ትንሳኤ የሰው የኃጢያት ዋጋ ተከፍሎ ክርቶስን የተቀበሉና በስሙ ያመኑ ሁሉ የክርስቶስን ሕይወት የተካፈሉበትና የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑበት ድል ነው። ትንሳኤ የእግዚአብሔር የብርታቱ ጉልበት የተገለጠበት ድል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ሲነሳ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ። (ኤፊ. 1:20-21) የእግዚአብሔር ቀኝ የሃይልና የድል ስፍራ ነው። ይህ ስፍራ ክርስቶስ በድል ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይ ሆኖ የተቀመጠበት ስፍራ ነው። ይህ ስፍራ ክርስቶስ በሰማይና በምድር ሁሉ አሁንና ለዘላለም ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ በድል የተቀመጠበት ስፍራ ነው። ትንሳኤ ክርስቶስ አለ ልክ ከፍ ከፍ ያለበት ነው። (ፊሊ. 2:9) ከዚህም የተነሳ በሰማይና በምድር ያለ ስም ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከካል። መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክራል። (ፊሊ. 2፡ 10-11)

ትንሳኤ ክርስቶስ ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ነው የሞትና የፍረሃት ቀንበር የተሻረልን። እርሱ ሞታችንን ሞቶ በትንሳኤው በሞት ላይ ስልጣን የነበረውን ዳቢሎስን ሻረው። በትንሳኤው ሃይል ወደ ክብር አመጣን። አዲስ ሕይወት እንድናገኝ ያደረገን ትንሳኤው ነው። አልዓዛርን ከመቃብር የጠራው ጌታ እኛንም በትንሳኤው ኃይል ከመቃብራችን አውጥቶ በህይወት ኑሩ አለን። ስለዚህ ኢየሱስ ከሙታን ስለትነሳ እኛም ደግሞ በትንሳኤ ኃይል እንድንኖር የትንሳኤ መንፈስ ተሰጠን። አሁን በኛ ውስጥ ያለውና በኛ የሚሰራው መንፈስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሳው የትንሳኤ መንፈስ ነው። ያ መንፈስ አሁን ለመንፈሳችን ትንሳኤን ሰጥቶታል። ለስጋችን ደግሞ የትንሳኤን ተስፋ አቀዳጅቶታል።

ትንሳኤ ታላቅ ነገር ስለሆነ ሁልጊዜ ጠላትን ያስደነግጠዋል። ክርስቶስ ተነስቶ መቃብሩ ባዶ በሆነ ጊዜ ዳያቢሎስ አናቱ ተመታ። ስለዚህም ኢየሱስ አልተነሳም ብላችሁ ዋሹ የሚል የውሸትን ድሪቶ ሰፋ። “እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት” ብላችሁ አስወሩ አለ። (ማቴ. 28:13) ስለዚህ ውሸት ልጄ በመገረም ዳዲ “ተኝተው ከሆነ እንዴት ተሰረቀ ለማለት ይችላሉ፤ የተኛ እንዴት የሚሆነውን ያውቃል” ብላ እንደታዘበችው ውሸቱ ለሕጻን እንኳ ስሜት የማይሰጥ ነበር። ነገር ግን የትንሳኤው ሃይል አሸንፎአል። ወሸት እውነትን ሊከድን አይችልምና፤ ጨላማም ብረሃንን ለመጋረድ አቅም የለውምና። ወገኖቼ፦ ኢየሱስ ተነስቷል። ለብዙዎችም ከትንሳኤው በኋላ ታይቷል። ለኛም ደግሞ ይህ የትንሳኤ ጌታ ተገልጦልናል፣ በርቶልናል። ኢየሱስ ከሙታን በመነሳቱም መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶናል። ዛሬ ትንሳኤውን በትንሳኤው ኃይል ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እናውጃለን። ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ፤ እኛንም አስነሳ። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page