top of page

ከሁሉም የሚበልጠው ትርፍ!

“ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ

ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማቴ16፡26)

የሰው ውሳኔዎች ሁሉ የምርጫው ውጤቶች ናቸው። ምርጫዎች ደግሞ ከትርፍና ከኪሳራ አንጻር የሚሰሉ ናቸው። በጊዜዓችን ወይንም በገንዘባችን አንድ ነገር ስናደርግ በዚያው ጊዜ ወይንም ገንዘብ ሌላ ነገር የማድረግ እድል አናጣለን። ስለዚህም ያለንን ሃብት (ችሎታ፣ እውቀት፣ ገንዘብ፣ ጊዜ... ወዘተ) ስንመነዝር በጣም ትርፋማ ነው በምንለው ነገር ላይ ማዋል ጥበብ ነው። ነገር ግን ትርፋማውን ለይቶ ማወቁ ላይ ነው ችግሩ። ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 16፡26 ላይ ስለ ትርፍና ኪሳራ ያስተማረው።

ሰው በአለም ላይ ያለውን ነገር ሁሉ የራሱ ቢያደርግና ለነፍሱ ግን ዋስትና ከሌለው ይህ ከመለኮታዊ ስሌት አንጻር ኪሳራ ነው። ለነገሩ ማንም ሰው አለሙን ሁሉ ለራሱ ሊያደርግ አይችልም እንጂ ቢችልና ቢያደርገው እንኳ በአለም ያለው ሁሉ የነፍሱን ዋጋ ሊተምን አይችልም። ቀላል ምሳሌ እንኳን እንውሰድ ብንል ዛሬ ከኛ ማን ነው ነፍሱን ስለ ሚሊዮን ዶላር የሚሰጠው? ማንስ ነው ቢችል ነፍሱን ለማትረፍ ሲል የሚጠየቀውን ማንኛውንም ዋጋ የማይከፍለው? የነብስ ዋጋ በአለም ሃብት አይተመንም። በአለም ካለው ሃብት ሁሉ ይልቅ በክርስቶስ ያገኘነው ደህንነት ይበልጣል።

ይህንን ክፍል ስናጤን ሕይወታችንን ከመለኮታዊ እቅድ አንጻር እንመራ ዘንድ ያሳስበናል። በምድር ያለው ነገር ሁሉ ጊዜያዊና አላፊ ነው። በክርስቶስ ያገኘነው ሕይወት ግን ዘላለማዊ ነው። ምናልባት በምድር ስንኖር በብዙ የተከናወነልን ልንሆን እንችል ይሆናል። ይህ ከሆነ እግዚአብሔር ይመስገን። የተሰጠንን መክሊት ለመንግስቱ ስራ፤ ለሰዎችም ጥቅም ልናውለው እንችላለን። ነገር ግን በምድር ያሰብነውን ያህል ወይንም የምንፈልገውንና የተመኘነውን ያህል የተሳካልን ባይመስለንም እንኳ የበለጠውን ትርፍ ስለያዝን ደስ ልንሰኝ ይገባል።

ወገኖቼ፡- ከዘላለም አንጻር የምድር ኑሮ ቅጽበታዊ ነች። በምድር ሰው ሲኖር አዳኝ የሆነውን ጌታ ኢየሱስን አግኝቶ ለነፍሱ ዋስትና ካለገኘ ምንም አይነት የተትረፈረፈ ምድራዊ ስኬት ውስጥ ቢኖርም እንኳ ጥቅሙ ትንሽ ነው። ለዚህ ነው ምድራዊ ህይወታችንን ከመለኮት አጀንዳ አንጻር በማየት፤ በዚህ አለም ጎደለ፣ ሞላ ከሚል ስሌት ባለፈ መልኩ መኖር ያለብን። ይህንን ነገር ስናስብ በትንቢተ ዳንኤል የተጠቀሱትን ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎምን እናስታውሳለን። ንጉሱ ላቆመው ምስል እንዲሰግዱ ሲጠየቁ የመለሱት መልስ የመረዳታቸውን ጥልቀት ያሳያል። እንዲህ ነበር ያሉት፡ “ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ” አሉት። (ዳን 3፡16-18) እግዚአብሔርን የምናመልከው በምድር ከሚሆኑ ነገሮች አንጻር አይደለም። እርግጥ ነው እግዚአብሔር ልጆቹን ይባርካል፣ ይታደጋል። ነገር ግን ቢሞላም ኢየሱስ ጌታ ነው። ቢጎድልም ኢየሱስ ጌታ ነው። ለኛ ትልቁ ትርፋችን የነፍሳችን መዳን ነው። እንደዚህ ደግም የእግዚአብሄርን ጽድቅና መንግስት እየፈለግን ስንኖር ሌላው ሁሉ (የምንፈልገው ሳይሆን የሚያስፈገን ሁሉ) እንደሚጨመርልን የጸና የተስፋ ቃል አለን። (ማቴ. 6፡33) አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page