የእግዚአብሔር ፍቅር።
- Redeatu G. Kassa
- Apr 28, 2018
- 2 min read
ፍቅር ጥልቅ ነገር ነው። ብዙ ጊዜ አንረዳውም ነገር ግን እንለማመደዋለን። ፍቅር አያስገድድም ነገር ግን ብርቱ ገፊ ነው። ከያኒያን ዜማን ከግጥም አዋህደው፤ ቀለም በቡርሽ አጣቅሰው፤ ድርሰት ከምናብ አፍልቀውና ምስል ከድምጽ አቀናብረው ስለ ፍቅር ጥልቀት፣ ጥንካሬና ውበት ይቀኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የፍቅርን ኃይል ሲገልጽ “ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና ... ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም”ይላል። (መኃ 8፡ 6-7) እግዚአብሔርም ሰውን የወደደበት ፍቅር እጅግ ብርቱና ጥልቅ ነው። እግዚአብሔር አንድ ልጁን ለመስቀል ሞት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ሰውን ሁሉ ወዷል። እግዚአብሔር እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ ሃጢያት የማያውቀውን አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለኛ በደል በመስቀል እንዲደቅና እንዲሞት በመፍቀድ ለእኛ ያለውን ወሰን የሌለውን ፍቅሩን አሳይቷል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል የሞተው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የለየውን የኃጢያት ግድግዳ በሞቱ አፍርሶ ለሚያምን ሁሉ የሚሆን የደህንነትን መንገድ ለማበጀት ነው። እግዚአብሔር ሰውን በምሳሌው ፈጥሮ እንዲበዛና ምድርን እንዲሞላት፣ ምድርንም እንዲገዛና እንዲያስተዳድር ባርኮት፣ ከእርሱም ጋር ሕብረትን እያደረገ በገነት እንዲኖር በክብር ስፍራ አስቀምጦት ነበር። ነገር ግን ሰው በዲያቢሎስ ተንኮል ተታሎ የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፍ መንፈሳዊ ሞትን ሞተ። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ኃጢያት ገባ። ከዚያም በኋላ የተከተለው የአዳም ትውልድ ሁሉ በኃጢያት ስር ወደቀ።
ጌታችን ኢየሱስ ከቅድስት ድንግል ማሪያም ተወልዶ በመስቀል ላይ የሞተው በኃጢያት ምክንያት የመጣብንን የሞት ፍዳ ለመክፈል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የአለምን ኃጢያት ሁሉ ተሸክሞ በመስቀል ላይ በመዋል፣ ስጋው ተቆርሶ፣ ደሙ ፈሶ ለአለም ሁሉ የሚሆን የደህንነት ቤዛ ሆኗል። በክርቶስም መስቀል በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የለየው ኃጢያት፣ በኃጢያትም ምክንያት በሰው ላይ ነግሶ የነበረው ሞት ተነስቷል። እግዚአብሔር በባህሪው ፍጹም ጻዲቅ ፍጹምም መሃሪ በመሆኑ የክርስቶስ ሞት የኃጢያትን ቅጣት በመክፈል የእግዚአብሐርን ጽድቅ ፈጸመ። የክርስቶስ ትንሳዔ ደግሞ የእግዚአብሔርን ምህረትና የማዳን ኃይል በመግለጽ ሙታን ለነበርን ለኛ የድነት መንገድ ሆነ። ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነን በሞቱና በትንሳኤው ስንተባበር ለኃጢያት ሞተን ለጽድቅ ህያዋን እንሆናለን።
እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀው ብቸኛው የመዳን መንገድ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” በማለት ይመክረናል። (ሐዋ. 4፡12) ጌታ ኢየሱስም “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ይህንኑ አረጋግጦልናል። (ዮሐ. 14፡6) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሚል “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6፡23)
ለደህንነት የሚያስፈልገውን ዋጋ ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍሎልናል። ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው በኛ ፋንታና በኛ ምትክ ነው። እኛ መሞት ሲገባን እርሱ ሞተ። በእርግጥም እግዚአብሔር ገና ኃጢያተኞች እያለን ወዶናል። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ይለናል። (ሮሜ 5፡8) እግዚአብሔር ታላቅ የፍቅር ግብዣ አድጎ እየጠራን ነው። የኛ ፋንታ ይህንን መድኃኒት ወስደን ከኃጢያት በሽታ መፈወስና የዘላለምን ሕይወት መቀበል ነው። ይህንን የመዳን ግብዣ ቸል ብንል ግን እድል ፋንታችን የዘላለም ሞት ይሆናል። እግዚአብሔር ልጁን እስከ መስጠት ወዶናል። ለፍቅሩ ምላሽ መስጠት የኛ ፋንታ ነው።
Comments