top of page

ምስጉን ማን ነው? — ሶስት

ባለፉት ሳምንታት እንዳየነው እግዚአብሔር ምስጉን የሚለው ሕዝብ አንደኛ በእርሱ የዳነውን ሕዝብ ነው። እንድዲሁም ደግሞ እግዚአብሔር ምስጉን የሚለው ሰው በክፉዎች ምክር እንደማይሄድ፣ በኃጢያተኞች መንገድ እንደማይቆም፣ በዋዘኞች ወንበርም እንደማይቀመጥ አይተናል። ይህንኑ ሃሳብ በመቀጠል ምስጉን ደስ የሚሰኝበትን ደግሞ እናያለን።

በመዝሙር አንድ ላይ እንደምናነበው ምስጉን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል። (ቁ. 2)ይህ ቃል የቀረበው ከቁጥር አንድ ጋር ተነጻጽሮ ነው። በቁጥር አንድ ላይ እንዳየነው ምስጉን በሃጢያተኞች ምክር፣ በመገዳቸውም እንዲሁም በዋዘኞች ወንበር ደስ አይሰኝም። ይልቁንም እግዚአብሔር ምስግጉን፣ ብሩክ የሚለው ሰው ደስታው በእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉን ሲሰማ ደስ ይለዋል፣ ቃሉን ሲያነብ ደስ ይለዋል፣ በቃሉ ምክር ደስ ይሰኛል። ልክ ዳዊት “ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” (መዝ. 119፡ 103) እንዳለ እንዲሁ እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ከምንም ነገር በላይ ቃሉን ይወዳል። ቃሉ የውስጥ ደስታና እርካታ ይሰጣል፤ ቃሉ ይፈውሳል። እግዚአብሔር የሰጠንም ውድ ነገር ቃሉ ነው።

ምስጉን በቃሉ ደስ ይሰኛል ደግሞም ቃሉን “በቀንና በሌሊት ያስባል።” (ቁ. 2) ቃሉን ማሰብ ቃሉን የመውደድ ውጤት ነው። ቃሉን ከወደድነው ቃሉን እንመገባለን። የተመገብነውን ደግሞ በውስጣችን አስቀምጠን እናስበዋለን። ማሰብ የምንችለው ያስገባነውን ነው። በውስጣችን የሌለውን ለማሰብ አንችልም። ቃሉን ማሰላሰል የጽድቅ መንገድ ነው። ንጉስ ዳዊት በመዝሙሩ“ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው” ይላል። (መዝ. 119፡ 9) እንዲሁም“አንተን እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” ይላል። (ቁ. 11) ጎልማሳ መንገዱ ንጹህ እንዲሆን(በጽድቅ እንዲመላለስ) ማድረግ ያለበት ቃሉን መመገብና ማሰላሰል ነው። እግዚአብሔር አምላክ በሙሴ እግር ተተክቶ የሕዝቡ መሪ ለሆነው ለኢያሱ የሰጠውም ትህዛዝ ተመሳሳይ ነው። ታላቅ ኃላፊት የተሰጠው ኢያሱ የተሰጠው መምሪያ አንድና ግልጽ ነው። እግዚአብሔር ለኢያሱ የሰጠው ትእዛዝ “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም” የሚል ነው።(ኢያ. 1:8) እንግዲህ ኢያሱ መንገዱ ሁሉ እንዲከናወንለት የተባለው ቃሉን ሁልጊዜ እንዲበላና እንዲያሰላስል ነው። በዚያ ውስጥ በጽድቅ መሄድ አለ፣ በዛ ውስጥ መታዘዝ አለ። በእግዚአብሔር ቃል መንገድ ስንሄድ ደግሞ መንገዳችን የመከናወን መንገድ ይሆናል።

በመዝሙር አንድ ላይም በእግዚአብሔር ቃል ደስ የሚሰኘውና ቃሉን በቀንና በሌሊት የሚስበው ምስጉን “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” (ቁ. 3) ተብልዋል። በእግዚአብሔር ቃል ደስ የሚሰኝ ሰው፣ ቃሉንም ሁልጊዜ የሚያሰላስል ሰው ፍሬያማ ነው። በእግዚአብሔር ወንዝ ይረሰርሳል። ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል። ከዚህም የተነሳ የመንፈስ ፍሬ ሁልጊዜ ያፈራል፣ ደግሞም ሁልጊዜ ደስተኛ ነው። ልምላሜን አያጣም። ወገኖቼ፦ እኛም በቃሉ ደስ እየተሰኘን፣ ቃሉን እየበላንና እያሰላሰልን ፍሬያማዎች እንሁን። ጌታ ከኛ ጋር ነው። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page