top of page

አምልኮ -- ትርጉም (አንድ)

የአምልኮን ትርጉም ከሚገልጹልን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ያደረገው ምልልስ አንዱ ነው። (ዮሐ. 4) በክፍሉ እንደምናነበው ጌታችን ከይሁዳ ወደ ገሊላ ለመሄድ ተነስቶ በሰማሪያ ማለፍ ግድ ሆነበት። (ቁ. 4) እንደ ዘመኑ ልማድና ባህል ከሆነ አንድ አይሁዳዊ በሰማሪያ አልፎ ወደ ገሊላ ከመሄድ ይልቅ በዙሪያ ጥምጥም መሄድን ይመርጣል። ምክንያቱም አይሁድና ሰማሪያዊያን የማይተባበሩ ስለነበር ነው። ጌታ ግን በሰማሪያ ማለፈን መረጠ። ይህ የጌታ አደራረግ በምሪት የሆነና የጠፋችን ነብስ ለማግኘት ባህሉ የደነገገውን ነውር በመስበር የተደረገ ነው።

ጌታ በሰማሪያ በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ውሃ ልትቀዳ በቀትር መጣች። በመሰረቱ በቀትር ውሃ አይቀዳም። ነገር ግን ሴቱቱ በማህበረሰቡ የተገለለች፣ የትዳር ችግር የነበረባት፣ በሕይወቷ እርካታ ያጣችና የተጠማች ስለነበረች ሌላ ምርጫ አልነበራትም። የሰፈርተኛውን አግቦና ስድብ ከመስማት ይልቅ ማንም በማያገኛት አደገኛ ሰዓት እንስራዋን ተሸክማ ውሃ ልትቀዳ መጣች። በዚያ ግን ያልጠበቀቸው ነገር ነው የገጠማት። ዛሬ የገጠማት ሰው የሚያገላት ሳይሆን ሊያናግራት የፈቀደና ውሃ አጠጪኝ ብሎ ጥማቷን ሊያረካ የመጣ ነው። ሴቲቱ ብዙ ጥያቄዎች ነበሯት። የጎሳ ግንኙነት ጥያቄ ነበራት። እንዴት አንድ አይሁዳዊ ወንድ ከሰማሪያዊት ሴት ጋር ይነጋገራል ትላለች። ደግሞም የታሪክ ትምክህት ነበራት። አባታችን ያዕቆብ የሰጠንን ውሃ ነው የምንጠጣው የምትል ነበረች። ደግሞሞ በሕይወት አለመርካት ችግር ነበራት። ብዙ ተጠምታለች፤ ብዙ ነገርም ሞክራለች ነገር ግን አልረካችም። በባሎች አልረካችም፣ በጎሳዋ አልረካችም፣ በታሪኳ አልረካችም፣ በአምልኮ ልምምዷም አልረካችም። ስለዚህ ጌታ የውስጧን ጥማት ገልጾ ሲያሳያት የአምልኮ ጥያቄዋን አነሳች። ምድንድን ነው ማምለክ? የት ነው የሚመለከው-- በተራራ ነው ወይንስ በኢየሩሳሌም፣ እንዴት ነው የሚመለከው? በማለት ጠየቀችው።

ጌታ ለዚህ ጥያቄ የሰጣት መልስ የአምልኮን ትርጉም ፍንትው አድርጎ ያሳየነናል። ጌታ አምልኮ ለሚያድነው ጌታ መስገድ ነው አላት። (ቁ. 22) አምልኮ ለእግዚአብሔር በፍቅር መገዛት ነው። አምልኮ እግዚአብሔርን መውደድ ነው። እውነተኛ አምልኮ በሕወታችን ለእግዚአብሔር የምሰጠው ስፍራ ነው። እግዚአብሔር በሕይወታችን አንደኛ (ቀዳሚ) ከሆነ እርሱን እያመለክን ነው። ነገር ግን በሕይወታን ከእግዚአብሔር ይልቅ ስፍራ የምንሰጠው ሌላ ነገር ካለ ጣኦትን እያመለክን ነው ማለት ነው። አምልኮ በልባችን ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ስፍራ ነው። አምልኮ እግዚአብሔር ከምፍራትና ከመውደድ የተነሳ ለእርሱ መቀደስ ነው። አምልኮ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ዋጋ ነው። የአምልኮ የእንግሊዘኛ አቻ ቃል “worship” የመጣው “worth ship”ከሚለው ኃረግ ነው። ይህም አምልኮ ማለት በሕይወታችን ለእግዚአብሔር የምሰጠውን ዋጋ መግለጽ እንደሆነ ያሳየናል።

ወገኖቼ፦ ኢያሱ እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን እንዳለ እኛና ቤታችንም በሕይወታችን እግዚአብሔርን በማስቀደምና የሚገባውን ስፍራ በመስጠት እርሱን የምናመልክ እንድንሆን የጌታ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሆን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page