top of page

የስልጣን ቃል

“... ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል...” (ማቴ 8፡9)

የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 8 በታምራት የተሞላ ነው። ክፍሉ የሚጀምረው ጌታ ኢየሱስ የተራራውን ትምህርት አስተምሮ ከተራራው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ እንደተከተለው በመግለጽ ነው። ባስከተልም ለምጻሙን ሰው ዳስሶ ሲፈውሰው እናነባለን። በመቀጠልም በቅፍርናሆም የመቶ አለቃውን አገልጋይ ፈወሰ። ከዚያም ጴጥሮስ ቤት ገብቶ በንዳድ የታመመችውን አማቱን አዳነ። አስከትሎም ብዙ ሰዎችን ከመናፍስት እስራትና ከደዌ ፈታ፣ መአበሉንና ወጀቡን በስልጣን ቃል አዞ ጸጥ አደረገው። ምእራፉ የሚጠቃለለው ኢየሱስ በጌርጌሲኖን በሁለት ሰዎች አድረው አገር የበጠበጡትን ክፉ መናፍስት አስወጣ። ክፍሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደዌ፣ በአጋንነትና በተፈጥሮ ላይ ጌታ መሆኑን ያስተምረናል። በጌታችን ፊት የሚቆም ምንም አይነት አጋንታዊም ሆነ ተፈጥሮዊ ኃይል የለም። በሽታ፣ አጋንንት፣ ባህርና ንፋስ ለእርሱ ይታዘዛሉ። ለዛሬ የጌታን የስልጣን ቃል አስምልክተን አገልጋዩ ከተፈወሰለት መቶ አለቃ አንጻር እንመለከታለን።

የቅፍርናሆሙ መቶ አለቃ በዙ መልካም ጎኖች ያሉት ሰው ነው። በመጀመሪያ ወደ ጌታ ሲቀርብ “ጌታ ሆይ” በማለት የጌታን ጌትነት በማወጅ ቀረበ። (ቁ. 6) ለአገልጋዩ ያሳየው ርሕራሔ አስገራሚ ነው። ግድ ብሎት ወደ ጌታ ያመጣው የአገልጋዩ ሕመም ነው። አገልጋዩ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሰቃየበት ነበር። በዘመኑ በነበረው ስረዓት ይህ መቶ አለቃ አገልጋዩን እንደማንኛው የመጠቀሚያ እቃ ሊቀቆጥረው፣ ከፈለገም ጥቅም እንደማይሰጥ ካሰበ ሊገድለውም ይችል ነበር። ነገር ግን ይህ መቶ አለቃ ስለአገልጋዩ ሕመም ወደ ጌታ መጣ። መምጣት ብቻ አይደለም ጌታንም ስለ አገልጋዩ ለመነ። (ቁ.7) ይህ ሰው ችግሩን በቤቱ ይዞ አልተቀመጠም። ነገር ግን የጓዳውን ችግር መፍተሔ ወደ ሚሰጠው ጌታ ይዞ መጣ። ወገኖቼ፦ ዛሬም ችግራችንን ይዘን ከማልቀስ ይልቅ ለችግራችን መፍተሔ ወዳለው ጌታ ዘውር ብንል ጌታ ፈጥኖ ይደርስልናል።

ሌላው የዚህ መቶ አለቃ አስገራሚ መረዳት ስለ ጌታ ቃል ያለው መረዳት ነው። ይህ መቶ አለቃ የጌታ ቃል የስልጣን ቃል እንደሆነ ተረድቷል። (ቁ. 9) ልክ እርሱ ከበላዩ ላሉት አዛዦች እደሚታዘዝና ከበታቹም ያሉት ጭፍሮች እንደሚታዘዙት እንዲሁ የጌታ ቃል የስልጣን ቃል እንደሆነ ተረድቷል። ለጌታ ቃል የማይታዘዝ፣ የጌታን ቃል የማይሰማ ፍጥረት እንደሌለ ገብቶታል። የጌታን ቃል ቦታና ጊዜ ሊወስነው እንደማችል አውቋል። የጌታ ቃል የሚሰራ ቃል፣ የሚፈጥር ቃል እንደሆነ አስተውሏል። ይህ መቼም አስደናቂ መረዳት ነው። ወገኖቼ፦ ዛሬም በእጃችን ያለው የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነው፤ የሚሰራ ነው። ቃሉ ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው። ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል። (ዕብ. 4፡12) ቃሉ መንፈስና ሕይወት ነው። ሕይወት ይሰጣል። የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በቃሉ ይገለጣል።

የመቶ አለቃው የቃሉን ኃይል የተረዳ ብቻ ሳይሆን አስደናቂ እምነትም የነበረው ሰው ነው። እምነቱ ጌታን አስደንቆታል። (ቁ. 10) መቼም ጌታን የሚያስደንቀው ነገር ቢኖር እምነት ነው። ጌታ በሚያምኑ ሰዎች ደስ ይለዋል። ቅዱሳን አባቶቻችንም የተመሰከረላቸው ስለ እምነታቸው ነው። ይህ መቶ አለቃ ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል አለ። ጌታ አንድ ቃል ከተናገረ ብላቴናው እንደሚፈወስ አምኗል። ጌታም “ሂድ እንዳመንህ ይሁንል አለው።” ይህ ቃል ከጌታ አንደበት በወጣበት ቅጽበት የዛ መቶ አለቃ ብላቴና ተፈወሰ። ወገኖቼ፦ የእግዚአብሔር ቃል የስልጣን ቃል ነው። በእምነት ስንቀበለው በሕይወታችን ድንቅ ነገር ይሰራል።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page