top of page

ልዩ መንፈስ -- ፈጽሞ መከተል!

“ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞቼ ግን የሕዝቡን ልብ አቀለጡ፤ እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ።” (ኢያሱ 14፡8)

የእግዚአብሔር ሰው ካሌብ ልዩ መንፈስ የነበረው ሰው ነው። ካሌብ የነበረው የልዩነት መንፈስ የእምነት መንፈስ ነው። ካሌብ በእግዚአብሔር ያመነ ብቻ ሳይሆን እግዚብሔርን ያመነ ሰው ነው። ይህ የልዩነት መንፈስ ደግሞ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ፈጽም የመደገፍ መንፈስም ነው። እንዲሁም ይህ ልዩ መንፈስ እግዚአብሔርን ፈጽም የመከተል መንፈስ ነው።

ካሌብ እግዚአብሔርን ፈጽም የተከተለ ሰው ነው። ይህንን ደግሞ ካሌብ እራሱ “እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ” (ቁ. 8) በማለት ያረጋግጥልናል። ይህ ደግም ካሌብ ስለ ራሱ ምስክርነት እየሰጠበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት የተገለጠ ነበር። ካሌብ እግዚአብሔርን ፈጽም በመከተሉ የሚረግጠው ምድር ሁሉ ለእርሱና ለዘሩ ርስት እንደሚሆን ሙሴ መስክሯል። (ቁ. 9) ሙሴ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርም እራሱ ካሌብ ፈጽም እንደተከተለው መስክሮለታል። (ዘኁ. 32፡11-12፤ ዘዳ. 1፡36) ከዚህም የተነሳ ትውልዱ ሁሉ በምድረበዳ ሲቀር ካሌብ ግን በሕይወት ቆይቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ገባ። ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ወሰደ። (ቁ. 14)

ካሌብ እግዚአብሔርን ፈጽም ነበር የተከተለው። እግዚአብሔርን የተከተለው በሙሉ ልቡ ነበር። ሁለንተናውን ለእግዚአብሔር የሰጠ ሰው ነው። ካሌብ ያልፍበት የነበረው ሁኔታና አካባቢው ልብን ሊከፍሉና ማመንታት ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ነበሩ። እርሱ ግን ከአስሩ ወገኖቹ ጋር ለአሰሳ በወጣ ጊዜ የተሰለፈው ከብዙሃኑ ሃሳብ ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ሃሳብ ጋር ነበር። አብረውት የወጡት አስሩን አልተከተለም። እንዲሁም ተስፋ የቆረጠውንም ሕዝብ አልተከተለም። እርሱ እግዚአብሔርን ተከተለ።

መከተል የራስን ሃሳብ በእግዚአብሔር ሃሳብ መጠቅለልን የሚጠይቅ ነው። በፈቃዱ ውስጥ መግባትን ይጠይቃል። ጌታችንም በወንጌላት ያስተማረን “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ነው። (ማቴ. 16፡24) የተጠራነው ጌታን እንድከተል ነው። የራሳችንን ፈቃድ እያገለገልን ጌታን ለመከተል አንችልም። መከተል መስቀልንም መሸከም ይጠይቃል። ነገር ግን ጌታን በፍጹም ልብ ስንከተል እንደ ካሌብ ከመልካም ነገር አንጎድልም። በህይወት እንኖራለን፤ ርስታችንን እንወርሳለን፤ በተስፋው ቃል ላይ እንደገፋለን፤ ሽምግልናችን በዘይት ይለመልማል። ወገኖቼ፦ በተሰጠን ዘመን ልክ እንደ ዳዊት የእግዚአብሔር ሃሳብ እንድናገለግል እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page