top of page

ስምህ ማነው? (ክፍል አንድ)

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ስሞች ብዙ ትርጉም ያላቸው እንደሆኑ ማየት እንችላለን። ለምሳሌ እግዚኣብሔር ዮሴፍን በብዙ መከራ ኣሳልፎት በልጅ ሲባርከው ልጁን ስም ሲያወጣለት እግዚኣብሔር መከራዬን ሁሉ የኣባቴንም ቤት ኣስረሳኝ ሲል ምናሴ ብሎ ጠራው። ሁለተኛ ልጁን ደግሞ እግዚኣብሔር በመከራዬ ኣገር ኣፈራኝ ሲል ኤፍሬም ብሎ ጠራው (ዘፍ. 41፡ 51-52)። ዛሬም የኔንና የናንተን መከራ ያስረሳንና በተቸገርንበትና መከራን ባየንበት ኣገር ፍሬያማዎች ያደረገን ጌታ ስሙ ይባረክ።

ስም ትርጉም ያለው ሲሆን ብዙ ጊዜ ደግሞ ከሰው ባህርይም ጋር የሚሄድ ነው። ለምሳሌ እግዚኣብሔር የኣብርሃምንና ሣራን ስማቸውን ሲለውጥላቸው የብዙዎች ኣባት እና የብዙዎች እናት የሚል ትርጉም ሰጥቶ ነው የቀየረላቸው (ዘፍ. 17:5)። እግዚኣብሔር እንደተናገረው ኣብርሃምና ሣራ የብዙዎች ኣባትና እናት በመሆን እንደተባረኩ እኛም በክርስቶስ በኩል የኣብርሃም ልጆች ስለሆንን ህያው ምስክሮች ነን።

ሌላው ስሙ የተቀየረለት ሰው ያዕቆብ ነው። በዘፍጥረት 32:27 ላይ እንደምናነበው ስምህ ማነው ብሎ ይጠይቀዋል። እርሱም ያዕቆብ ነኝ ኣለው። ያዕቆብ ማለት ኣታላይ ማለት ነው። ያዕቆብ እንደስሙም በባህርይውም ኣታላይ እንደነበረ እናውቃለን። ወንድሙን ዔሣውን በምስር ወጥ ኣታሎ በኩርናውን ከመውሰዱም በላይ ኣባቱን ይስሃቅንም ኣታሎ የወንድሙን በረከት የቀማ ሰው ነው። የትም ፍጭው ዱቄቱን ኣምጪው እንደተባለው ኣባባል በረከት ይሁን እንጂ በማንኛውም መንገድ ማግኘት ኣለብኝ ብሎ በማመን በራሱ ጥበብና መንገድ በመጓዝ ላይ ያለ ሰው ነው። ይሁን አንጂ ይህ ማታለሉ ብዙ ዋጋ ኣስከፍሎታል እንጂ ሊያረካው ኣልቻለም። ከዚህም የተነሳ ለብቻው ባለበት እግዚኣብሔር ኣገኘውና ሌሊቱን ሙሉ ሲታገለው አንደቆየ እናነባለን (ዘፍ32፡ 24)። ከዚህ በኋላ ነው ስምህ ማነው ሲለው ስሜ ያዕቆብ ነው። ኣታላይ ነኝ። ብሎ እውነቱን ሲመልስለት ልክ ነህ እስካሁን የኖርከው ኑሮ የማታለል ነበር ካሁን በኋላ ግን ስምህ እስራኤል ይባል ከእግዚኣብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ ኣሸንፈሃልና። በማታለል መንገድ ሳይሆን እውነተኛ በረከትን የሚባርከው እግዚኣብሔር እንደሆነ በመገንዘብ ሳይታከት ሌሊቱን በሙሉ ከጌታ ጋር ሲታገል ወይም ሲጸልይ እንዳሳለፈና ካልባረከኝ ኣልለቅ ህም ብሎ ሲያመር እናያለን።

እንግዲህ እውነተኛ በረከት የሚመጣው በጽድቅ መንገድ በመጓዝ ከኣምላክ ዘንድ እንጂ በራሳችን ጥበብና ለሥጋ በሚመች በኃጢኣት መንገድ እንዳይደል ልንገነዘብ ይገባናል። ስምህ ማንው ብሎ ጌታ ሲጠይቀን ባህርያችንን ሳንደብቅ ልንነግረው ይገባናል። ኃኪም ቤት ሄዶ ለኃኪሙ በሽታውን የደበቀ ሰው ትክክለኛ መድኃኒት እንደማያገኝ ሁሉ እኔና እናንተም ባምላካችን ፊት ማንነታችንን በግልጽ በመናገር የነፍስ ፈውስ እንድናገኝ ጌታ ይርዳን። (ይቀጥላል)


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page