top of page

አመስጋኙ ሳምራዊ።

በሉቃስ 17 ላይ አስገራሚ ታሪክ እናነባለን። ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በገሊላና በሰማሪያ መካከል አለፈ (ቁ. 11)። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙ አስር ለምጻሞች ተገናኙት። እዚህ ጋ ልብ የምንለው በብሉይ ኪዳን ስርዓት በለምጽ የተመታ ሰው እንደ እርኩስ ስለሚቆጠር ከለምጹ እስኪነጻ ድረስ ከማህበረሰቡ ተለይቶ ነበር የሚኖረው። ለዚህም ይመስላል እነኚህ አስር ለምጻሞች ወደ ጌታ ሳይቀርቡ በርቀት የቆሙት። ለምጻሞቹ ወደ ጌታ ለመቅረብ አልደፈሩም ነገር ግን በሩቅ ቆመው “ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ ማረን” እያሉ ጮሁ። ችግረኞችን አይቶ የማያልፈው ጌታ ወደ እነርሱ ተመለከተ። “ሂዱ ራሳችሁን” ለካህናት አሳዩ” አላቸው። ለምጻሞቹም ቃሉን ይዘው እንደ ስረዓቱ ራሳቸውን ለካህናት ለማሳያየት ሲሄዱ ሳለ ነጹ። የነጹት አስሩም ናቸው። ነገር ግን መፈወሱን አይቶ ለምስጋና የተመለሰው አንዱ ብቻ ነበር። ለማመስገን ስለተመለሰው አንዱ ቃሉ ሲናገር “ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ” (ቁ. 15-16) ይለናል። ይህ ሳምራዊ ከፈውሱ በላይ የፈወሰውን ጌታ አከበረ። ዘጠኙ ግን የፈለጉት ጌታን ሳይሆን ፈውሳቸውን ብቻ ነበር። ጌታ የተደነቀው ሊያመሰግን በተመለሰው ሳይሆን ፈውሳቸውን ይዘው ለምስጋና ባልተገኙት ዘጠኙ ነበር። ጌታ እንዲህ ጠየቀ፡ “አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ” (ቁ. 17-18)። ሊያመሰግን የተመለሰው ሳምራዊ የስጋን ፈውስ ብቻ ሳይሆን የነፍስ መዳንም እንደሆነለት ከቃሉ እናነባለን። ጌታ ሳምራዊውን አመስጋኝ “ተነሳና ሂድ እምነትህ አድኖሃል” አለው (ቁ. 19)። ለሳምራዊው በእምነት የሆነለት መዳን ከስጋው ፈውስ ያለፈ ነበር።

እኛም ከአመስጋኙ ሳምራዊ የምንማራቸው ብዙ ቁብ ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፦ ይህ ሰው የተደነቀው በፈውሱ ሳይሆን በፈወሰው ጌታ ነበርና ለማመስገን ተመለሰ። እኛም ከተደረገልን ይልቅ ያደረገልን ጌታ ላይ አይናችን ሲያርፍ በምንም ሁኔታ አመስጋኞች እንሆናለን። ሁለተኛ፦ ምስጋናው ያልተቆጠበ ነበር። በታላቅ ድምጽ፣ አለ ይሉኝታ ነበር እግዚአብሔርን ያመሰገነው። “ለምጻም ነበርኩ። እግዚአብሔር ፈወሰኝ። እግዚአብሔር ይመሰግን። ከሰው የቀላቀለኝ አምላክ ይባረክ” እያለ ጮኸ። ይህም ሳይበቃው በጌታ እግር ፊት በግንባሩ ወድቆ ሰገደ። እኛም በሙሉ ኃይላችን ስለተደረግልን ሁሉ ሳንቆጥም የምናመሰግን መሆን ይገባናል። ሶስተኛ፦ የምስጋናው ኃይል ጌታን አንቀሳቀሰው። ሰውዬው በምስጋናው ውስጥ እምነቱን ገለጸ፤ ፈውሱ ወደ እምነት አመጣው። በስጋው ፈውስ ተደንቆ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን የዘላለም ደህንነትንም አገኘ። እግዚአብሔር ይመስገን። እኛም በምስጋና ስንሞላና እግዚአብሔርን ስናመሰግን ከድል ወደ ድል እንሻገራለን። ቃሉም እንደሚለን የምስጋና መስዋዕትን የሚሰዋ እግዚአብሔርን ያከብራል። በዛም ውስጥ የሚበልጠውን የግዚአብሔርን ማዳን ያያል። (መዝ. 50:23) አመስጋኞች እንሁን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page