top of page

ምስጋና የድል መንገድ።

“ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ።” (መዝ. 50፡23)

ምስጋና እግዚአብሔርን የምናከብርበት መንገድ ነው። ምስጋናችን በፊቱ እንደሚያርግ መስዋዕት ለእግዚአብሔር የመአዛ ሽታ ነው። በምስጋና ውስጥ ደግሞ የደህንነት መንገድ አለ። እግዚአብሔርን ምስጋናን ለሚሰዋ ማዳኑን፣ ምህረቱን፣ እርዳታውን ይለግሳል። ምስጋና ዘርፈ ብዙ ነው፤ በዋናነት ግን ስናመሰግን ሶስት ነገሮችን አንዳደርጋለን።

(1) ስናመሰግን እግዚአብሔር ላደረገልን ነገር እውቅና እየሰጠን ነው፦ እግዚአብሔር ከቁጥር በላይ የሆነ ነገር አድርጎልናል። መዳናችን ቀዳሚ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እኛ ሁላችን ሙታን ነበርን። ደግሞም በጨለማ ነበርን። ሕይወትን ያውም የዘላለም ሕይወት ስለሰጠን ሁልጊዜ ልናመሰግነው ይገባናል። በጨለማችንም ላይ ታላቅ ብረሃን በርቷል። መዳን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጆችም ሆነናል። ልጅነታችን ውስጥ ብዙ የከበረ ነገር አለ። ልጅነታችን ውስጥ የእግዚአብሔር አባትነት አለ፤ የእግዚአብሔር ፍቅር አለ፤ ወደ እርሱ አለመከልከል መቅረብ አለ እንዲሁም በእርሱ ደስታ ውስጥ መግባት አለ። ልጆች ብቻ ሳይሆን ያደረገን ደግሞም ለአገልግሎት ሾሞናል። በፊቱ ጉድ፣ ጉድ የምንል ባለማረጎች ተደርገናል። የክህነት ቅባት ፈሶብን፤ የክህነት ልብስ ለብሰናል። በምድር ሕይወታችንም ባርኮናል። ብዙ የምንቆጥራቸው በረከቶች አሉን። ታዲያ ይህንን ሁሉ ላደረገልን ጌታ ነብሳችን ማመስገን እና ውለታውን መቁጠር አለባት። ይህ እግዚአብሔርን ማክበር ነው።

(2) ስናመሰግን የእምነት ቋንቋ እየተናገርን ነው፦ በምስጋና ውስጥ እምነት አለ። የሚያመሰግን ሰው ከሁኔታዎች ሁሉ በላይ እግዚአብሔርን ከፍ ያደርጋል። አንዳንድ ጊዜ የምናልፍባቸው ሁኔታዎች ለማመስገን ላይመቹ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር ይመሰገናል። እማባቆም እንደተቀኘው የበረቱ ቦዶ መሆን፣ የእርሻው መጉደል ምስጋናንን መቀነስ የለበትም። በዚያም ውስጥ እርሱ ጌታ ነው። ጳሎስና ሲላስ በወህኒው የውስጠኛው ክፍል ምስጋና ሲሰው የእምነትን ቋንቋ እየተናገሩ ነበር። ከእስራቱና ከእንግልቱ እግዚአብሔር ይበልጣል እያሉ ነበር።

(3) ስናመሰግን በጠላታችን ላይ መንፈሳዊ ውጊያ እየከፈትን ነው፦ እግዚአብሔር ሲመሰገን ጠላት ይዋረዳል። ዳዊት እንደ ዘመረው ከአፋችን የሚወጣው ምስጋና ቂመኛ የሆነውን ጥላታችንን ዲያቢሎስን ይመታዋል። (መዝ.8፡2) ምስጋናና መንፈሳዊ ውጊያ ጎን ለጎን ናቸው። የእግዚአብሔር ህዝብ ምስጋና “በጕሮሮአቸው ነው፤ ሁለት አፍ ያለውም ሰይፍ በእጃቸው ነው።” (መዝ. 149፡ 6) ምስጋና ሲቀድም ጠላት ይመታል።

ወገኖቼ፦ ለእግዚአብሔር የምስጋናን መስዋእት እንሰዋ እንጂ ምስጋናን የምናጓድል አንሁን። ምስጋናችን እጁን ታንቀሳቅሳለች—ማዳኑን ታመጣለች።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page