ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም!
የያዕቆብን ታሪክ ስንማር ከላይ በርዕስነት የመረጥኩትን ወሳኝ የሆነና ቁርጠኝነትን የሚያመላክት ባለሁለት ቃላት ሓረግ እናያለን (ዘፍጥርት 32፣26)።
ለያዕቆብ መባረክ ማለት በብረሃናት አምላክ ህልውና ውስጥ ዉሎ ማደር መሆኑን የተረዳበት ወቅት መሆኑን ያስረግጥልናል። የአምላካችን የመዳኒታችንን ፈቃድ መረዳት፣ የእሱን ባህርይ ተካፋይ መሆንና ሰላማችንን የሰላም ልኡል፣ አባትንትን ከዘላላም አባት፣ ኃይልን ከኃያል አምላክ፤ ምክርን ድንቅ መካር ከሆንው ከኢየሱስ ብቻ አግኝተን መባረክ እንደምንችል በተረዳ ጊዜ ያዕቆብ ካልባረከኝ አልለቅህም እንዳል አስባለሁ፤ እረዳለሁም።
በልጆች፣ በንብረት፣ በጤና እና በእድሜ መባረክም በረከት ነው። ነገር ግን ያዕቆብ ካልባረከኝ አልለቅህም ሲል ሁለት ሚስቶች፣ አስራ አንድ ልጆች፣ ጓዝም ነበረው። ያንን ሁሉ ወደፊት ከላከ በኋላ እውነተኛ በረከት በሰማያው በረከት መባረክ መሆኑን ነፍሱ ስትረዳና ስትገነዘብ ለሊቱን በሙሉ ሲታገል አድሮ ካልባረከኝ አልለቅሁም እንዳለም ይገባኛል።
ደግሞም የያዕቆብንም ቀደምት የህይውት ጉዞ ስንመለከት ወንድምን የማታለል፣ ወደ ላባ መሸሽ፣ ደግም ከላባ ቤት መኮብለልና በአጠቃላይ ስጋት የበዛበት መሆኑን እንረዳለን። እናም እድሜውን ሙሉ የለፋበትን የደከመላቸውንና የደከመባቸውን ሚስቶቹን፣ ልጆቹንና ሃብት ንብረቱን የያቦቅን ወንዝ አሻግሮ ከሰደዳቸው በኋላ የመባረክ ሚስጥር የተገለጠለት ይመስለኛል።
በመሆኑም ለሊቱን በሙሉ ሳይታክት ታግሎ ነው እንግዲህ “ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ” የሚል ቃል ከአምላኩ አንደበት እንዲወጣ የሆነው። ያቆብም በተራው ያለ የሌለ ሃይሉን አሰባስቦ “ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም!” አለው።
ያቺ ንጋት የያዕቆብን ስም እስራኤል አደረገችው።
የያዕቆብም ስም እስራኤል የመባሉ ሚስጢር ያዕቆብ የበረከት ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር እንደሆነ በመገንዘቡና ወደ ተስፋይቱም ምድር ለመግባት የተቃረበ በመሆኑ እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም በመለወጥ እንደ አገልጋዩ እንደሚያየው ያስታወቀበት ንጋት ነበረች።
ስለዚህ እኔና ቤቴ እንደ ያዕቆብ “ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም!”እያልን የእግዚአብሄርን ፊት እየፈለግን አዲሱን አመት እንጠባበቃለን። ሁላችንም “ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም” በሚል ብርቱ ጸሎት የእግዚአብሔርን ፊት እንፈልግ ዘንድ ይገባናል። አዲሱ አመት ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት የምንባረክበት አመት ይሁንልን። ተባረኩ።