top of page

የጌርጌሴኖኑ ምስክር

ጌርጌሴኖን በሚባል ከተማ የሚኖር አንድ በአጋንት እስራት ውስጥ የነበረ ሰውን ታሪክ በማርቆስ 5 ላይ እናነባለን። ይህ ሰው በታላቅ ስቃይ ውስጥ ነበር። የሚኖረው ከሰው ተለይቶ በመቃብር ስፍራ ነበር። በሰንሰለትና በእግር ብረት ሊታሰር አልቻለም። በውስጡ ባለው አጋንታዊ ኃይል የታሰረበትን ሰንሰለት ይበጥሳል፤ የእግር ብረቱንም ይሰባብራል። ስለዚም ማንም ሰው የማይቀርበው ኃይለኛ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን በርሱ ያለው አጋንንት ሌትና ቀን ያስጮኸው ነበር። ሰውነቱንም በድንጋይ ይጭር ነበር። ይህ በዚህ ታላቅ እስራት የነበረ ሰው ጌታ ወደዚች ከተማ ሲመጣ ሮጦ ሰገደለት። በውስጡም ያለው አጋንንት መለፍለፍ ጀመረ። አጋንቱ ስሙን በተጠየቀ ጊዜ ብዙ በመሆኑ ሌጌዎን ነን በማለት መለሰ። ከታሪኩ እንደምናነበው ጌታ አጋንቱን ወደ እርያዎች መንጋ እንዲገቡ ሲያዛቸው ቁጥራቸው ሁለት ሺህ የሚሆን የእርያ መንጋ እየተጣደፉ ወደ ባሕር ገብተው ሞቱ። በዚህ ሰው ውስጥ ለካ ከሁለት ሺህ በላይ አጋንት ሰፍረው ኖሯል ያስጨንቁት የነበሩት። ጌታ ሲደርስለት ግን ከእስራቱ ተፈታ። እንደ ሰው ልብስ ለበሰ። ልቡም ተመለሰለት። ይህ ታላቅ መፈታትን ያገኘ ሰው ያደረገው ነገር አስደናቂ ነው። የከተማው ሰዎች የሆነውን ነገር ሰምተው በፍርሃት ጌታን ከከተማቸው እንዲወጣ ለመኑት። ጌታ እንደ ጥያቄአቸው ከከተማቸው ለመውጣት “ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው” ቁ. 18። ይህ ሰው የሚገርም ነገር ነበር የገባው። በምንም ሁኔታ ከጌታ መለየትን አልወደደም። ከመከራው ካሳረፈው፣ ከሰው ከቀላቀለው ጋር መሆንን ፈለገ። ምናልባትም እንደ ሰው ቆጥሮ ያዘነለት ጌታ ብቻ ነበር። በመቃብር የተጣለ፣ ለሰንሰለትና ለእግር ብረት ያልተበገረ፣ ሳያቋርጥ የሚጮህና ራሱን በድንጋይ እየባጠጠ ለሚኖር ለዚህ አሳዛኝ ሰው ጌታ ነጻነትን ሰጠው። ሌጌዎን በጌታ ፊት መቆም አልቻለምና እየተጣደፉ በባህር ሰጠሙ። ኢየሱስ ጌታ ነው! ጌታ ግን ይህ ሰው አብሮት እንዲሄድ አልፈቀደለትም። ይልቁንም ስራ ሰጠው። ጌታ “ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው” ቁ. 19። ይህ ሰውም ጌታ እንዳዘዘው ሄዶ “ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ” ቁ. 20። ይህ ሰው የተደረገለትን አስደናቂ ምስክርነት እየተናገረ መስበክ ጀመረ። ምስክር ሆነ። እንዴት ያለ ድንቅ ሽግግር ነው። ስብከቱ ሌላ ነገር አልነበረም ጌታ ለእርሱ ያደረገለትን ታምራትና ድንቅ መናገር፤ የተቀበለውንም ምህረት ማውራት ነበር። በከተሞች እየዞረ ኢየሱስ አድኖኛል እያለ መሰከረ። ብዙዎችንም ደረሰ። ወገኖቼ፦ እኛም ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራንን የጌታንን በጎነት እንድንናገር የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ነን (1ጴጥ. 2፡ 9)። ለእያንዳንዳችን የተደረገውን ድንቅ ነገር እየተናገርን ምስክሮች ለመሆን ተጠርተናል። ምስክር ያየውንና የቀመሰውን ነበር ይናገራል። እኛም ጌርጌሴኖኑ ሰው ጌታ ያደረገልንን እንናገር። ጌታ ይባርካችሁ።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page