top of page

ተባርከናል!!!

ምድራዊ ሕይወት በረከትን ለመያዝ የሚደረግ ሩጫ የበዛበት ነው። ሰዎች የባለጠግነትን በረከት ለማግኘት ይጥራሉ፤ ዝናንም ለማግኘትም ብዙ መንገድ ይሄዳሉ፤ የስልጣንምም እርከን ለመውጣት ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋሉ። በብዙ ሃይማኖቶችም ሰዎች የጽድቅን በረከት ያገኙ ዘንድ ስረአቶችን ለመፈጸም ይታገላሉ። ሰው በራሱ በረከትን ለማግኘት የሚያደርገው መውተርተር የበረክት ጫፍ ላይ አድርሶ የሚሳርፍ አይደለም። ይልቁንም በብርቱ ጥረትና ግረት የያዙት ነገር ሲጨብጡት ምንም እየሆነባቸው ሌላ ከፍ ያለ የበረክት መሰላል ላይ ለመውጣት ያልማሉ። ፍላጎታቸውም እንደ የሚሸሽ ኢላማ ከፊታቸው አያመለጠ ይቀድማቸዋል። አንድ ጊዜ እውቁ ቱጃር ጆን ዲ ሮክፌለር ለአንድ ሰው ምን ያህል ገንዘብ ይበቃዋል ተብለው ሲጠየቁ “ባለህ ላይ ጥቂት ሲጨማር” በማለት መመለሳቸው ይነገራል። ምድራዊው ሰው ሁልጊዜ ባለው ላይ ጥቂት መጨመር ይፈልጋል። የፈለገውን “ጥቂት” ሲጨምር ደግም ሌላ “ጥቂት” መጨመርን ይሻል። እንዲህ እያለ ሰው የማይሞላ የበረከት ቋት ሊምላ ሲዳክር ሕይወቱን ይፈጃል።

ክርስትና ግን የሚጀምረው “ትባረካለህ” ብሎ ሳይሆን “ተባርከሃል” ብሎ ነው። ክርስትና በረከትን የመፈለግ ሩጫ ሳይሆን እንደተባረክን ተረድተን፤ የበረከታችንን ጥልቀትና ብዛት እየተረዳን በምድር እግዚአብሔር እንድፈጽመው የሰጠንን ስራ እየሰራን መኖር ነው። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር እስራኤልን “አንተ ብሩክ ነህ፣ እግዚአብሔር ያዳነው ሕዝብ እንዳንተ ያለ ማን አለ?” (ዘዳ. 33፡29 አ.መ.ት.) ይለዋል። የእስራኤል በረከት የእርሱ ጥረት ውጤት ሳይሆን በእግዚአብሔር የመመረጡ ጉዳይ ነው። የሕዝቡ በረከት እርሱ እራሱ እንጂ በእርሱ ያገኙት የምድር ሲሳይ አልነበረም። ስለዚህም “መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፤ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው” ይለዋል። (ቁ. 27) አዲስ ኪዳንም የሚያስተምረን እግዚአብሔር“በመንፈሳዊ በረክት ሁሉ” በሰማያዊ ስፍራ እንደ ባረከን ነው። አሁን ተባርከናል! ከዚህ በኋላ የሚያስደንቀን ነገር ቢኖር የበረክቱ መገለጥ ነው። የተባረክንበት የበረከት ጥልቀት አሁን ካለን የመረዳት አቅም የሚያልፍ ነው። ነገር ግን አንድ ነገር እናውቃለን። እኛ በረከትን ለማግኘት የምንውተረተር አይደለንም። በክርስቶስ ተባርከናል። የምድር ሁኔታችን ምንም ይሆን ምን የተባረክን ሰዎች ነን። በረከታችን እሩሱ እራሱ ነው። ለዚህም ነው ቃሉ እርሱን ማለትም መንግስቱንና ጽድቁን እንድንሻ የሚመክረን። በሰማይ በረከት የባረከን አምላክ በሚያስፈልገን የምድር በረከት አያጎድለንም። ምድራዊው ነገር ቢጎድልም እንኳ እንባቆም እንድዘመረው መንፈሳዊ በረከታችንን እያየን በመስጋና ሙላት ውስጥ እንዳንገባ አይከለክለንም።

ወገኖቼ፦ የተባረከ ሕዝብ አመስጋኝ ነው። ለዚህም ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ ምንም እንኳ ይህንን መልዕክት ሲጽፍልን በእስር ላይ ቢሆንም “የባረከን ይባረክ” ብሎ ለምስጋና የሚጋብዘን። እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብሩክ ነው። የበረከት ቁንጮ ላይ ደርሷል። ስለዚህም የበረከቱን አምላክ በምንም ሁኔታ ውስጥ ያከፍራል። እግዚአብሔር በረከቴ ነው ስንል ስለ “አሳው” አይገደንም፤ ካስፈለገ መረባችን እስቂቀደድ ይሞላዋል። ንጉሱ ዳዊት እንደዘመረው እግዚአብሔር እረኛችን ነው። የሚያሳጣን የለም። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page