top of page

የተለየ ሕዝብ

“እናንተ ግን ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፤

የንጉሥ ካህናት፤ ቅዱስ ሕዝብ ፤ ለእርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ።” (1ኛ ጴጥ. 2፡9)

እግዚአብሔር አባታችን ምን ዓይነት ሹመት እንደሰጠንና እርሱ እንዴት እንደሚያየን ማስተዋል

ለትክክለኛ የእምነት አቋም ወሳኝ ነው። በምድር ላይ ካሉት ሰዎች በሙሉ እግዚአብሔር በጸጋው የለየን

ሕዝብ ነን። ይህ ደግም እኛ እንደፈለግነው፣ እንደሚሰማንና እንደሚታየን እንድንኖር ሳይሆን በምድር

ያለነው በዓላማ እንድንኖር ነው። ንጉስ ዳዊት በዘመኑ የእግዚአብሔርን ሃሳብ እንዳገለገለ እኛም በዘመናችን

የእርሱን በጎነት ለማወጅ ተጠርተናል።

አምላካችንና አባታችን በፀጋ በጌታ ኢየሱስ ልጆቹ ካደረገን በኋላ ወደ እውነት የሚመራውን

መንፈስ ቅዱስን በውስጣችን አኖረው። እግዚአብሔር በፍጥረት መጀመሪያ የፍጥረቱ በኩራን ከነበሩት

ከአዳምና ከሔዋን ጋር የነበረውን አይነት ኅብረት ከእያንዳንዱ በጌታ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት አድርጎ

ከወለዳቸው ልጆቹ ጋር እንዲኖረው ይፈልጋል። ለዚሁም ሁልጊዜ በፊቱ እንድነገኝ እጅግ ይሻል። በጸሎት

ፊቱን በመሻትና ሕያው ቃሉን በመመገብ ከእርሱ ጋር የጠበቀና የማያቋርጥ ኅብረት ሲኖረን እርሱን በበለጠ

ክብር እናየዋለን፤ ኃይልን እንቀበላለን፤ በአእምሮአችንም መታደስ እንለወጣለን። ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ

እንዳስተማረን በአእምሮአችን መታደስ ስንለወጥ የእግዚአብሔር ፍቃድ ምን እንደሆነ ፈትነን እናውቃለን

ደግሞም የዓለምን አስተሳሰብ በመናቅ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እናድጋለን። (ሮሜ. 12፡1-2)

በመጽሐፈ በመሳፍንት ምዕራፍ 6 ላይ ስንመለከት ጌዲዮን የሚባለው ሰው እራሱን

የሚመለከተው ፈሪ፤ ነገሮች ያልተሳኩለት፤ ሁል ጊዜ ተገዝቶ የሚኖር፤ የበታች የሆነ ሰው አድርጎ ነበር።

ከሁሉ የሚገርመውና የሚያሳዝነው የእስራኤል ሕዝብ የአምላካቸውን ቃል ካለመፈለግ የተነሳ

በምድያማውያን መገዛታቸውንና መጠቃታቸውን አለማስተዋሉና በበለጠ ደግሞ ከነሙሴና ከእነ ኢያሱ ጋር

የነበረው ኤልሻዳዩ አላካቸው ኃይሉ እንዳልቀነሰ ገልበቱ እንዳልላላ፤ ማስተዋሉም ዛሬም የማይመረመር

መሆኑን መዘንጋቱ ነው። እግዚአብሔር ግን በዚህ ሰው ውስጥ የተመለከተው ጽኑና ኃያል የሆነ የእስራኤል

አዳኝ ነበር። እንዲሁም ሙሴ የታየው የእርሱ ኮልታፋነት ሲሆን እግዚአብሔር ግን የታየው ሕዝቡን

ከፈረዖን እጅ ነፃ የሚያወጣ የእርሱን የጊዜው መሳሪያ ነበር። ዳዊት በሌሎች የታየው እንደ አንድ የበጎች

እረኛ ሲሆን እግዚአብሔር ግን የታየው አንድ የሕዝቡ የጊዜው ታዳጊ ነበር። እግዚአብሔር በያንዳንዳችን

ውስጥም የሚያየው ለእርሱ አላማ ለመኖር የተለዩ፤ የእርሱን በጎነት የሚያውጁ ቅዱሳን ወንድና ሴት

ልጆችን ነው።

ቅዱሳን ወንድሞችና እሕቶች፦ እኛስ እራሳችንን እንዴት ነው የምናየው? ምንም ሁኔታ ይሁን፤

የበረታ የጠላት ጦር ይሁን፤ ድል የተነሳው ዲያቢሎስ ይሁን ከእነርሱ ጋር ያለው ኃይል፣ ጥበብና እውቀት

ከእኛ ጋር ካለው ከኤልሻዳዩ አምላካችን አይበልጥም። ሁሉም ያሉት በጊዜአቸው ለእኛ ትምህርት ሆነው

ሊሸነፉ ነው። በጌታ ኢየሱስ የዳነ ሰው አሸናፊ ነው። እኛ ልንገዛ፣ ልንበዛ፣ ለበረከት፣ የምድር ጨውና

ብረሃን ለመሆን ከማይጠፋ ዘር ተወልደናል። ለተፈጠርንበት ዓላማ ለመኖር የሚያስፈልገን ሙሉ ጸጋና

ሥልጣን ተሰጥቶናል። በተጨማሪም ጌታን እንደ ግል አዳኝ አድርገን ስንቀበል የጥበብ፣ የማስተዋል፣

የዕውቀት፣ እንቆቅልሽን የመፍታትና የገዥነት መንፈስ ተሰጥቶናል። እግዚአብሄር እውነተኛ ማንነታችንን

በመረዳት ይባርከን። እኛም በመረዳትና በውሳኔ ይህንን የተጠራንበትን የድል ሕይወት በሥልጣን እንኑር።

አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page