top of page

የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ

በዮሐንስ ምእራፍ ሁለት ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀምርያውን ምልክት ሲያደርግ እናነባለን። አውዱ የሰርግ ሥነ-ስርአት ነው። ቦታው በገሊላ አውራጃ ቃና በምትባል ከተማ ነው። በዚህ ሰርግ ላይ ጌታችንና ደቀ መዛሙርቱ እንዲሁም እናቱ ቅድስት ማርያም ታድመዋል። በባህላችን እንደሚደረገው ሁሉ በአይሁድ ባህልም ሰርግ ደግሶ መዳር፤ እንግዶችን ጋብዞ ማብላት የተለመደ ነው። በዚህ ሰርግ ላይ ሽር ጉድ እያሉ የሚያስተናብሩ አገልጋዮች አሉ። መለስ ቀለስ እያሉ የጎደለውን ይሞላሉ፣ ከማጀት ወደ እልፍኝ፤ ከእልፍኝ ወደ ማጀት ተፍ ተፍ እያሉ ታዳሚውን ያስተናግዳሉ። ደግሞም በሰርጉ የከበሩ ሰዎችም ታድመዋል። የከተማው አስተዳዳሪ (ከንቲባ) በዚያ አለ። ታዳሚው ብዙ ይመስላል። ደግሞም ደጋሾች አሉ። “ብሉ እንጂ፣ ጠጡ እንጂ” እያሉ ፈካ ብለው በታዳሚው መካከል ይመላለሳሉ። በዚህ መኃል ነው እንግዲህ የደጋሾቹ ወይን ጠጅ አለቀ የሚለው አስደንጋጭና አሳፋሪ ነገር ብቅ ያለው። በዚህ ችግር ወቅት እናቱ ቅድስት ማሪያም ካደረገችው ነገር ብዙ ቁም ነገሮችን እንማራለን።

አንደኛ እናቱ ቅድስት ማርያም ችግሩን ወደ ጌታ ወሰደችው። ቅድስት ማርያም የወይን ጠጁ ማለቁን በሰማች ጊዜ ችግሩን እያሰላሰለች አልተቀመጠችም። ወይንም በችግሩ ግራ ተጋብታ እምታደርገው አልጠፋትም። ይልቁንም የችግሩ መፍተሄ እንዳለው በልቧ ወዳመነችው ወደ ጌታ ኢየሱስ አመጣችው። “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ወገኖቼ ይህ ትልቅ ማስተዋል ነው። የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሙን ምንድነው የምናደርገው? ለችግሩ መፍተሄ ለማግኘት ወደ ማን ነው የምንሄደው? ከጌታ እናት ከቅድስት ማርያም የምንማረው አንዱ ትልቁ ነገር ማንኛውም ችግር ሲገጥመን መፍተሄ በጁ ወዳለው ጌታ ይዘነው እንቅረብ። አንድም ችግሩን ከፊታችን ያነሳዋል አለያም በችግሩን የምናልፍበትን ጸጋ ይሰጠናል።

ሁለተኛ እናቱ ቅድስት ማርያም በድግሱ ስፍራ ለነበሩት አገልጋዮች “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚልን ምክር ሰጠቻቸው። ይህ ግሩም፣ በማስተዋል የተሞላ አስደናቂ ምክር ነው። እርሱ የሚላችሁን አንዱንም ሳታስቀሩ አድርጉ። ምናልባት የሚላችሁ አሁን ላይገባችሁ ይችላል ነገር ግን አድርጉት። ቅድስት ማርያም ጌታ የሚለውን በማድረግ ውስጥ የችግሩ መፍተሔ እንዳለ አስተውላለች። ወገኞቼ፦ ዛሬም እኛ ጌታ በቃሉና በመንፈሱ የሚለንን ሁሉ ብናደርግ መፍተሔ እናገኛለን። በቃሉ ውስጥ የጌታ ድምጽ አለ። በቃሉ ውስጥ ፈውስ አለ። በቃሉ ውስጥ ምክር አለ። በቃሉ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ይሰራል። ቃሉን ስንታዘዝ መከናወን እናገኛለን።

በሶስተኛ ደረጃ ከዚህ ክፍል የምንማረው የገጠመንን ማናቸው ነገር ይዘን ወደ ጌታ ስንቀርብ ከሁኔታው ጌታ የሚከብርበት የከበረና የላቀ ነገር ይወጣል። ቅድስት ማርያም የደጋሾቹን ችግር መፍተሄ ወዳለው ጌታ አመጣችው። እርሱም ደግም ትእዛዝ ሰጠ። አገልጋዮቹም የሚላቸውን አደረጉ። ውጤቱ አስደናቂ ነበር። የሆነው ነገር የችግሩ መቃለል ብቻ ሳይሆን ከዛ ችግር የከበረ ነገር ወጣ። የሚበልጥ ጣእም ያለው የወይን ጠጅ ወጣ። ጌታ የከበረበት ነገር ወጣ። ወገኖቼ፦ በእኛም ህይወት እንዲሁ ነው። አለቀ፣ አበቃ ያልነውን ነገር ወደ ጌታ ይዘነው ስንቀርብ ለመደነቂያ የሚሆንን ነገር ጌታ ከዛ ነገር ውስጥ ያወጣል። በምንም ሁኔታ ተስፋ አትቁረጡ ነገር ግን የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ ወደ ጌታ አምጥታችሁ በግሩ ስር ጣሉት። መፍተሔ ከጌታ ዘንድ ይወጣል። ክብር ሁሉ ለጌታ ይሁን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page