top of page

የኤልሳዕ አጥንት! የኤልሳዕ አጥንት!

ከጥቂት አመታት በፊት በሃገራችን በጣም የታወቀ ስመጥሩ አገልጋይ ጌታን እንዴት

እንደተቀበለ ሲናገር በስደት ከሃገር ለመውጣት ጅቡቲ እያለሁ ወችማን ኒ (Watchman Nee)

የተባለው የእግዚአብሔር ሰው የጻፈውን መጽሐፍ አነበብኩ ፤ ያ መጽሐፍ ለኔ እንደ ኤልሳዕ

እጥንት ሆኖ በድኔን አስነሳው አለ። እንደምታስታውሱት ነብዩ ኤልሳዕ ከሞተ በኋላ መቃብሩ

አጠገብ ሰዎች እንድ የሞተ ሰው ሊቀብሩ ሲሉ አ ደጋ ጣዮችን አይተው በመፍራት ሬሳውን

በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት። ያ በድን የኤልሳዕን አጥንት ሲነካ የሞተው ሰው ድኖ በእግሩ

ቆመ። (2 ነግ 13፡21 ) ይህ የአገራችን እውቅ አገልጋይ የወችማን ኒን መጽሐፍ ከኤልሳዕ አጥንት

ጋር ነው ያነፃፀረው። የኤልሳዕ አጥንት በድን እንዳስነሳ እንዲሁ ፡ የወችማን ኒ መጽሐፍ በወቅቱ

በመንፈስ ሙት ለነበረው ሰው የእግዚአብሔርን እውነት በመግለጽ ከሞት ወደ ሕይወት

እንዲሸጋገር ረዳው። በኤልሳዕ አጥንት ውስጥ አልፎ የእግዚአብሔር መንፈስ የሞተን ሰው ሕያው

እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁ በተፃፈው ወችማን ኒ መጽሐፍ ገፆች ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ አልፎ

ለዚህ ሰው ሕይወትን ሰጠው። በእርግጥም የወችማን ኒ መጽሐፍቶችን ያነበባችሁ ወይንም

የምታነቡ ይህ እያልኩት ያለሁት ነገር ምን እንደሆነ ይገባችኋል። የእግዚአብሔር ሰው ወችማን ኒ

የጻፏቸው መጽሐፎች ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስለሚያስተላልፉ

የሰዎችን ሕይወት ይነካሉ።

ወችማን ኒ አስደናቂ ሕይወት ያላቸው ክርስቲያን ነበሩ። በትውልዳቸው ቻይናዊ ሲሆኑ

ጌታን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉት በ17 ዓመታቸው ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ

ህይወታቸውን ለጌታ አገልግሎት ሰጥተው ኖረዋል። በቻይና ኮሚኒስቶች አለቅጥ ተሰቃይተዋል።

የእድሜያቸውን የመጨረሻ 20 ዓመታት ያሳለፉት በእስር ነበር። ወችማን ኒ የስነ-መለኮት

ትምህርት ቤት ገብተው አልተማሩም ነገር ግን አስደናቂ የክርስትና መርህ መጽሐፍትን

አበርክተዋል። ሃምሳ የሚሆኑት መጽሐፍቶቻቸው ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉመዋል። መጽሐፍ

ቅዱስን በጥልቀት በግላቸው ከማጥናት በተጨማሪ 3000 በላይ የሚሆኑ መጽሐፍትን ያነበቡ

ሲሆኑ ፡ የገቢውንም አንድ ሶስተኛ የሚያጠፉት በመጽሐፍት ላይ ነበር። (ሌላውን እንድ ሶስተኛ

ሌሎችን ለመርዳት ሲጠቀሙ የሚኖሩት በቀሪው አንድ ሶስተኛ ነበር)።

የወችማን ኒን ታሪክ ያነሳነው የመጽሐፍትን ጉልበት ለማሳየት ነው። የኛ ሕዝብ የማንበብ

ባህል የለውም ይባላል። ይህ መቼም ትልቅ ጉድለት ነው። ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።

ብዙ ነገር የምናውቀው በትምህርት ቤት አይደለም ይልቁንም በማንበብ ነው። በተለይም እንደ

ክርስቲያን የማንበብ ባህል ሊኖረን ይገባል። ቅዱሳን ሰዎች የሚጽፉት መጽሐፍት የእግዚአብሔር

መንፈስ ይተላለፍበታል። እንዲሁም ደግሞ አንድ መጽሐፍ ማለት የአንድ ሰው የሕይወት ዘመን

ልምድና ማስተዋል የታጨቀበት ነው። መጽሐፍትን በማንበብ ልምዶችን ማግኘት ፡ ሌሎች

ባህሎችን ለመረዳት እንችላለን። እንደ ክርስቲያን የአምላካችንን ፍቃድ ፡ ሃሳብ ፡ ትእዛዝ ወዘተ

የምናውቀው ቅዱስ ቃሉን በማንበብ ነውና በርትተን ማንበብን እራሳችንን እናስለምድ።

ጌታ ይርዳን እላለሁ። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page