top of page

የመንፈስ ቅዱስ የስራ ዘመን ነው።

ባለፈው ሳምንት በነበረን ኮንፈራንስ ላይ እግዚአብሔር “ይህ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ የስራ ዘመን” እንደሆነ ተናግሮናል። መንፈሳችንንም በዚህ ዙሪያ ሲያነቃቃው ነበር። እውነት ነው ይህ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ነው። አሁን ከቤተ ከርስቲያን ጋር ሆኖ አብና ወልድን እያከበረ ያለው መንፈስ ቅዱስ ነው። ጌታ ኢየሱስ የምድር አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ አባቱ ከመሄዱ በፊት ለደቀመዛሙርቱ የሰጣቸው ትልቁ ተስፋ መንፈስ ቅዱስ ነው። ጌታ እንዲህ አላቸው፡ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐ. 14፡ 15-17) በዚህ ቃል ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ የምንማራቸው በርካታ ነጥቦች አሉ።

በመጀምሪያ መንፈስ ቅዱስ ለዘላለም ከኛ ጋር ነው። ጌታ ኢየሱስ በምድር ለተወሰኑ አመታት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተመላልሷል። እስከ መስቀል ሞት ድረስ በመታዘዝም የአባቱን ፈቃድ ፈጽሞ ለደህንነታችን ቤዛ ሆኗል። አሁን ደግሞ በክብር ከፍ ከፍ ብሎ በአብ ቀኝ አለ። እኛንም የልጅነትን ስልጣን ሰጥቶን ከርሱ ጋር በአብ ቀኝ በከበረ ስፍራ አስቀምጦናል። ነገር ግን አሁን ጌታችን ዳግመኛ መጥቶ ቤተ ክርስቲያንን እስኪወስዳት ድረስ ከኛ ጋር ያለው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ ከኛ ጋራ ነው። አሁን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ይሰራል። ሙሽራይቱን ለክርስቶስ አያዘጋጀ አብሯት እስከ መጨረሻው ይቆያል።

ሁለተኛው ሃሳብ መንፈስ ቅዱስ እንደ ጌታ ኢየሱስ ያለ ሌላ አጽናኝ መሆኑ ነው። “አጽናኝ” -- Comforter -- ፒራቅሊጦስ-- Counselor የሚለው ቃል “ረዳት፣ በሁሉም ጉዳይ የምንፈልገው፣ የምናማክረው፣ የምንጠይቀው” ማለት። ጌታ በምድር በነበረበት ጌዜ የቃሉን ሚስጠር እየገለጠ፣ በአጋንንት የተያዙትን ነጻ እያወጣ፣ ድዊያንን እየፈወሰ፣ የመንግስቱን ወንጌል እየሰበከ በአጠቃላይ የአባቱን የአብን ፍቃድ እያደረገ ተመላልሷል። ሐዋሪያቱና ደቀ መዛሙርቱ በሁሉ ነገር ዘወር ብለው ይመለክቱ የነበረው ጌታን ነው። እምነታቸው ሲናወጥ ወደ እርሱ ተመልክተው ይጽናናሉ። ጥያቄ የሆነባቸውን ነገር ሁሉ ወደ እርሱ ያቀርባሉ። መንፈስ ቅዱስ “ሌላ አጽናኝ” ሆኖ ይህንን ስራ ለመቀጠል ነው የመጣው። ሐዋሪያቱ በነገር ሁሉ ወደ ጌታ ዘወር ይሉ እንደነበር እኛም በነገር ሁሉ ወደ መንፈስ ቅዱስ ዘወር እንል ዘንድ ያስፈልገናል።

ሶስተኛው ሃሳብ መንፈስ ቅዱስ የእውነት መንፈስ መሆኑ ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራል። (ዮሐ. 16:13) መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስን ማንነት፣ አዳኝነትና ትንሳኤ እየመሰከረ ሰዎችን እውነት ወደ ሆነው ክርስቶስ ይመራል። የግዚአብሔርን እውነት በአማኝ ልብ በማብራት የቃሉን መገለጥ ይሰጣል። መንፈፈስ ቅዱስ ባለበት እውነትና ብርሃን ስለሚገለጥ ሰዎች በቃሉ ኃይል እየተነኩ ለመዳን ምን እናድርግ እያሉ ወደ እውነት ምንገድ ይመጣሉ።

የመጨረጫው በዚህ ክፍል ያለው ሃሳብ መንፈስ ቅዱስ ከኛ ጋር እና በኛ ውስጥ መሆኑ ነው። መንፈስ ቅዱስን አለም ሊያውቀው አይችልም። እኛ ግን እናውቀዋለን። በውስጣችን ነው፤ አብሮን ነው። እኛ የእርሱ መቅደሶች ነን። በምንገባበትና በምንወጣበት ሁሉ ይህንን የክብር መንፈስ ይዘን እንንቀሳቀሳለን። ይህ የክብር መንፈስ አምላክ ነው፣ ፈጣሪ ነው፣ ህይወት የሚሰጥ ነው፣ ቅርጽ ለጠፋበት አለም ቅርጽ የሚሰጥ ነው፣ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ነው፣ ለአገልብሎታችን ደግሞ ኃይል የሚሰጠን ነው፣ በድንቅና በታምራትም ስለ ኢየሱስ ትንሳኤ የሚመሰክር ነው። ማን በውስጣችን እንዳለ እናስተውል ይሆን? ለጌታ ለመንፈስ ቅዱስ እውቅና እየሰጠን እንመላለስ።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page