መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ምስክር።
“ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል::” (ዮሐ. 15:26)
ይህ ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ነው። መንፈስ ቅዱስ አሁን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሆኖ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክራል። መንፈስ ቅሱስ የጌታ ኢየሱስን ማንነት ይመሰክራል፤ የጌታ ኢየሱስን ትንሳኤ ይመሰክራል፣ የጌታን አዳኝነት ይመሰክራል። ያለ መንፈስ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ መመስከር አይቻልም። ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ለአገልግሎት ከመውጣታቸው በፊት መንፈስ ቅዱስን እንዲጠብቁ ትዕዛዝ የሰጣቸው። መንፈስ ቅድስን ከተቀበሉ በኋላ ምስክሮች እንደሚሆኑ አረጋገጠላቻው። “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” አላቸው። (ሐዋ. 1:8) መንፈስ ቅዱስ ዋናው ስራው ስለ ኢየሱስ መመስከር ነው። እኛም መንፈስ ቅዱስን ስንምላ የኢየሱስ ምስክሮች እንሆናለን። በመንፈስ ቅዱስ የሚደረጉት ታአምራቶችም በዋናነት ፋይዳቸው ሰዎች ወደ ኢየሱስ እንዲመጡ ማገዝ ነው።
መንፈፈስ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ማንነት ይመሰከራል። ኢየሱስ በመጀመሪያ የነበረ ነው -- ጅማሬ የለውም። እርሱ ከአብ ጋር ነበር -- ስብእና ያለው ነው። እርሱ እግዚአብሔር ነው -- ኢየሱስ መለኮት ነው። (ዮሐ. 1:1) ቃሉ “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” እንደሚለ ሁሉ የተፈጠረው በርሱ ነው — እርሱ ፈጣሪ ነው። (ቁ. 2) አሁንም ያለውን ፍጥረተ አለም በስልጣኑ ቃል ደግፎ የያዘው እርሱ ነው። (ዕብ. 1:3) እርሱ የሕወት ምንጭ ነው። በእርሱ ሕይወት አለ። ከእርሱ ውጭ ሕይወት የለም። የመጣው ም ሕይወት እንዲሆንልን፣ እንዲበዛልንም ጭምር ነው። (ዮሐ. 10:10) ኢየሱስ የመገለጥ ሁሉ ምንጭ ነው። የአለም ብርሃን ሆኖ የመጣው እርሱ ነው። በርሱ በኩል የመጣው ብርሃን ደግሞ ጨለማን ሁሉ የሚያሸንፍ ብርሃን ነው። በዚህ ብርሃን ፊት የሚቆም የጭለማ ኃይል የለም። ወደ ኢየሱስ ስንቀርብ ጨለማ ይበተናል -- ስፍራ ይለቃል። ስለዚህም “ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም” (ዮሐ. 1:5)። ኢየሱስ በስጋ የተገለጠው መልኮት ነው -- ቃልም ስጋ ሆነ። (ቁ. 14) መንፈስ ቅዱስ ይህንን የኢየሱስን ማንነት ይመሰክራል።
መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን አዳኝነት ይመስክራል። የመንፈስ ቅዱስ አንዱ ስራው አለምን ስለ ኃጢያት መውቀስ ነው። (ዮሐ. 16:8) መንፈስ ቅዱስ በሚሰራበት ስፍራ ሁሉ ሰዎች በንስሃ እየተመለሱ የጌታን አዳኝነት ይቀበላሉ። በበአለ ኅምሳ ጊዜ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የኢየሱስን ትንሳኤ በስልጣን ሰበከ። ኢየሱስን “እግዚአብሔር ... የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና” በማለት ትንሳኤውን አወጀ። (ቁ. 24) ኢየሱስን “እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን” በማለት ትንሳኤውን አበሰረ። (ቁ. 32) በአብ ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ተቀብሎ ለቤተ ክርስቲያን እንዳፈሰሰው ተናገር። በዚህ ጊዜ ይሰሙት የነበሩት ሁሉ ልባቸው ተነካ። መንፈስ ቅዱስ ወደ ልባቸው ደረሰ። ስለዚህም ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ብለው ጠየቁ። ጴጥሮስ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” በማለት ደህንነትና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መሰከረላቸው። ቃሉን የሰሙና የተቀበሉ ሁሉ ዳኑ፣ ተጠመቁ። ሶስት ሺ ነብሳት ተጨመሩ። መንፈስ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ አዳኝነት የመሰክራል። (ይቀጥላል)