top of page

መንፈስ ቅዱስ የትንሳኤው ምስክር።

“ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፦ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።” (ዮሐ. 7:37-39)

ባለፈው ሳምንት እንዳየነው መንፈስ ቅሱስ የጌታ ኢየሱስን ማንነትና አዳኝነት ይመሰክራል። በዛሬው መልዕክት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ የክርስቶስ ትንሳኤ ምስክር እንደሆነ እንመለከታለን። ጌታ ኢየሱስ በላይ የሰፈረውን ቃል የተናገረው የዳስ በዓል የመጨረሻና ታላቁ ቀን ላይ ነው። የዳስ በአል የደስታና የምስጋና በአል ነው። እስራኤላዊያን ይህንን በዓል የሚያከብሩት መክር ከሰበሰቡ በሁኋላ አምላካቸውን በደስታ ለማመስገን ነው። (ዘዳ. 16:15) ልምላሜንና ፍሬአማነትን ለማመልከት ዳስ ሰርተው ዳሱን በለመልሙና ፍሬያማ በሆኑ ቅጠሎች ይቸፉኑታል። (ዘሌ. 23:39) ከዛም በአምላከቸው ፊት ሰባት ቀን ደስ ይላቸዋል። (ቁ.40) የበዓሉ የመጨረሻ ቀን በዓሉ በብዙ ምስጋና የሚጠናቀቅበት የደስታ ጥግ ያለበት የሃሴት ቀን ነው። በዚህ የበዓሉ ቁንጮ ቀን ኢየሱስ ቆሞ በታላቅ ድምጽ ጮሆ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ” ሲል አወጀ። ከበዓሉ አውድ አንጻር ይህ ግር የሚል ነገር ነው። በዚህ የዳስ በዓል የመጨረሻ ቀን ጥማት ያለ አይመስልም፤ ከዛ ደስታ ያለፈ ምንም ነገር ያለ አይመስልም። ነገር ግን ኢየሱስ የሚበልጥ ነገር፤ ያልተደረሰበት ነገር ለተጠሙ ሁሉ የሚሰጥ የከበረ ስጦታ እንዳለ አበሰረ።

ይህ የከበረ ስጦታ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። ኢየሱስ እንደገለጸው መንፈስ ቅዱስ በኛ ውስጥ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ነው። ይህ ወንዝ ከሰማይ ምንጭ ሳያቋርጥ የሚፈስ ሕይወትን የሚሰጥና የሚያድስ ምንጭ ነው። ምንጩ በውስጣችን ነው። ከውስጣችን እየፈለቀ ወደ ውጪ ይፈሳል። ሲፈስ ደግሞ ልምላሜንና ህይወትን እየሰጠ ይፈሳል። ይህ ሃሳብ በሕዝቅኤል 47 ላይ ከምናነበው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከሚወጣው ውሃ ጋር ይመሳሰላል። ልክ የመንፈስ ቅዱስ ወንዝ ከሆዳችን እንደሚፈልቅ ውሃው የሚወጣው ከመቅደሱ ውስጥ ነው። የውሃው ኃይል እየጨመረ እንደሚሄድ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስም ስራ በሕይወታችን እየበዛና እያደገ የሚሄድ ነው። ውሃው በሚያልፍበት ሁሉ ልምላሜና ሕይወት እንደሚሆን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በሚሰራበት ሁሉ ፈውስና ሕይወት ይሆናል። ኢየሱስ የዚህን የአዲስ ኪዳን ተስፋ ትልቅነትና ብልጫ ለማጽናት ቆሞ፣ ጮሆ ተናገረ። ማናችንም ቸል ልንለው የማይገባን ታላቅ ስጦታ ነው። መንፈስ ቅዱስን ሁልጊዜ፣ በየቀኑ መጠማት አለብን።

ቢዚህ ክፍል የወንጌሉ ጸሐፊ ሐዋሪያው ዮሐንስ ጌታ በዚህ ስፍራ የተናገረው በእርሱ የሚያምኑት ሊቀበሉት ስላለው ስለ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያብራራል። ደግሞም “ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበር” ይለናል። ክፍሉ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠን ኢየሱስ ስለከበረ እንደሆነ ያስረዳናል። ይህንን ደግሞ በሐዋ. 2 ላይ ከተጻፈልን ጋር አገናኝተን ስናነበው የኢየሱስ መክበር በትንሳኤ መነሳቱ እንደሆነ እንገነዘባለን። በሐዋ. 2:32-33 ላይ ሐዋሪያው ጴጥሮስ የኢየሱስን ትንሳኤ ከመንፈስ ቅዱስ መምጣት ጋር አገናኝቶ ሰበከ። “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው” ይለናል። ወገኖቼ፦ የአብ ተስፋ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ለቤተ ክርስቲያን የላከው ሞትን አሸንፎ በትንሳኤ ከፍ ከፍ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ በታላቅ ትንሳኤ ባይነሳ ኖሮ መንፈስ ቅዱስ አይመጣም ነበር። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የመጣው ኢየሱስ ስለከበረና ይህንኑ እውነት ለመመስከር ነው። ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ትንሳኤ ይመሰክራል።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page