top of page

መንፈስ ቅዱስ የኃይል መንፈስ።

“... መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ...” (ሐዋ. 1:8)

መንፈስ ቅዱስ የኃይል መንፈስ ስለሆነ በመንፈስ ቅዱስ ስንሞላ ኃይልን እንቀበላለን። መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ኃይል በተለያየ መንገድ የሚገለጥ ነው። በላይ በሰፈረው ክፍል ቃሉ መንፈስ ቅዱስ በኛ ላይ ሲወርድ ኃይልን እንደምንቀበል ይናገራል። አያይዞም ደግሞ ይህ የሚሰጠን ኃይል ምስክሮች እንደሚያደርገን ይናገራል። መንፈስ ቅዱስ ከተሞላን በኋላ የጌታ ምስክሮች እንደምንሆን ይናገራል። ሁለት ነገሮች በዚህ ክፍል እንመለከታለን። በመጀመሪያ መንፈስ ቅዱስን ስንቀበል አለምንም ቅድመ ሁኔታ የጌታ ምስክሮች እንሆናለን። መንፈስ ቅዱስን ተቀብለን ስለ ጌታ ምስክሮች አለመሆን አንችልም። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ስለ ጌታ የሚመሰክር ስለሆነ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ጌታ ሲናገር “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ” ብሎናል። (ዮሐ. 15፡ 26-27) መንፈስ ቅዱስ ስለ ጌታ የሚመሰክር በመሆኑ እኛም ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ስለ ጌታ አብረን እንመሰክራለን። ሁለተኛው ከክፍሉ የምናስተውለው ሃሳብ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ኃይል እያደገና እየሰፋ የሚሄድ እንደሆነ እናያለን። ሐዋሪያቱ እንደመጣላቸው ቃል ምስክርነታቸው ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በይሁዳና በሰማሪያ ዘልቆ እስከ ምድር ዳር እንደ ሄደ ሁሉ እኛም በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነታችን እያደገና እየበዛ የሚሄድ ይሆናል። እንግዲህ የምናስተውለው የመጀመሪያው ነጥብ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ኃይል ምስክሮች እንደሚያደርገን ነው።

መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ኃይል በተግዳሮት ፊት በጽናት ለመቆም የሚያስችለን ነው። በሐዋሪያት ስራ ምዕራፍ አራት ላይ ስናነብ ጴጥሮስና ዮሐንስ በቤተ መቅደስ ደጃፍ የነበረውን ከመወለዱ ጀምሮ አንካሳ የነበረውን ሰው በጌታ በኢየሱስ ስም ከፈወሱት በኋላ በወቅቱ የነበሩት የኃይማኖት መሪዎች ተነሱባቸው። እንዲያውም በጌታ በኢየሱስ ስም ዳግመኛ እንዳይናገሩ በከፍተኛ ዛቻ አስፈራርተው ለቀቋቸው። ይህንንም ጉዳይ ይዘው ቅዱሳን በአንድ ልብ ወደ ጌታ በጸሎት ቀረቡ። ጸልየው ሲጨርሱ “ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ” (ሐዋ. 4:31)። መንፈስ ቅዱስን እንደገና ከተሞሉ በኋላ ሐዋሪያቱ ቃሉን በግልጽ ተናገሩ። ይህ የሚያሳየን ከገጠማቸው ተግዳሮት በኋላ በጸሎት መንፈስ ቅዱስን ተሞልተው እንደገና ቃሉን በኃይል እንደ ሰበኩ ነው። “በግልጽ ተናገሩ” የሚለው ኃሳብ የሚያሳየው ቃሉን ያለፍርሃት፣ በድፍረት መናገራቸውን ነው። መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በስልጣንና በድፍረት እንድንናገር ኃይልን ይሰጠናል። ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስንናገር የሚቋቋመን አይኖርም። ለዚህ ነው ስለ እስጢፋኖስ ቃሉ ሲመሰክር “ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም” የሚለን። (ሐዋ. 6:10) ጌታም እንደሰተን የተስፋ ቃል በመንፈስ ቅዱስ ስንሞላ “ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ” እንቀበላለን። (ሉቃ. 21:15)

ወገኖቼ፦ መንፈስ ቅዱስ የኃይል መንፈስ ነው። ለክርስቶስ ምስክሮች እንድሆን ኃይል ይሰጠናል፤ ደግሞም በተግዳሮት ፊት በጽናት የሚያቆም ኃይል የሰጠናል።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page