top of page

የትውልድ ባላደራነት።

ከቤተ ክርስቲያናችን ራዕይ መካከል አንዱ “በእምነት ጠንካራ፣ በአእምሮ ደግሞ የላቁ ልጆችን ማሳደግ” ነው። ልጆቻችን በእምነት የጠነከሩ ሆነው እንዲያድጉ መትጋት አለብን። የዚህ ትጋት አቅጣጫ ደግሞ ልጆቻችን እግዚአብሔርን በግል እንዲያውቁና እንዲወዱ መርዳት ነው። ለዚህ ቁልፉ ነገር አዘውትረን ለልጆቻችን መጸለይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማርና ከቅዱሳን ልጆች ጋር ሕብረት እንዲኖራቸው ማመቻቸት ነው። እንዲሁም ልጆቻችን በእውቀትና በጥበብ ልቀት እንዲኖራቸው መቅረጽ ይገባናል።

እግዚአብሔር ቃሉን ለልጆቻችን እንድናስተምር አዟል። እግዚአብሔር ለሙሴ “ሕዝቡን በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ” ብሎ ተናግሮታል (ዘዳ. 4:9-10)። ከዚህ ክፍል እንደምንረዳው እግዚአብሔር ቃሉን ለልጆቻችን እንድናስተምር አዟል። ይህንን ደግሞ የምናደርገው ልጆቻችን እግዚአብሔርን መፍራት ይማሩ ዘንድ ነው። እንደዚሁም እግዚአብሔር ለእስራኤል “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው” ሲል አዟል (ዘዳ. 6፡ 6-7)። እንደዚሁም የእግዚአብሔር ቃል ስለ ልጅ አስተዳደግ መመሪያ ሲሰጠን “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ይለናል። (ምሳሌ 22:6) ልጆቻችንን በሚሂዱበት መንገድ የምንመራብት ዋናው መንገድ ለልጆቻችን የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር ነው። ልብ እንበል -- ይህ ኃላፊነት በዋናነት የቤተ ክርስቲያን ኃላፊትነት ሳይሆን የወላጅ ኃላፊነት ነው። ለልጆቻችን የእግዚአብሔር ቃል ስናስተምር ልጆቻችን እግዚአብሔርን በቃሉ ወደ ማወቅ ይመጣሉ፤ እንደ ቃሉም የሆነ የጽቅን አቋም ይይዛሉ። ለዚህ በጣም ጥሩ ማስረጃ የሚሆኑን ዳንኤልና ጓደኞቹ ናቸው። እነ ዳንኤል ወደ ባቢሎን በምርኮ ተውስደው በገጠማቸው ተግዳሮት ሁሉ ውስጥ በጽናት እግዚአብሔርን አስከብረው ለመቆም የቻሉት ከልጅነታቸው ጅምረው የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ተማሩና በቃሉ እግዚአብሔርን ስላወቁት ነው። ዮሴፍም እንደዚሁ ለገጠመው የኃጢያት ግብዣ እንቢ እንዲል ያስቻለው “በእግዚአብሔር ፊት” ይህንን እንዴት አደርጋለሁ ከሚለው እግዚአብሔርን ከማወቅ ከመጣው የጽድቅ አቋሙ የተነሳ ነው።

ልጆቻችን በአእምሮ ልቀትም ምሳሌ መሆን አለባቸው። እነ ዳንኤል በጥበብና በመረዳት የሚቋቋማቸው አልነበረም። ንጉሡ በተነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ እነ ዳንኤል ያለ አልተገኘም። በጥበብና በማስተዋል ሁሉ ከሌሎቹ ከእነርሱ ጋር ከነበሩት ሁሉ አስር እጅ በልጠው ተገኙ (ዳን. 1፡ 19-20)። ይህ ሊሆን የቻለው እግዚአብሔር ለብላቴኖቹ“በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን” ስለሰጣቸው ነው። (ቁ. 17) እውነት ነው እግዚአብሔር ለልጆቹ የጥበብንና የማስተዋልን መንፈስ ይሰጣል። በተጨማሪም እግዚአብሔር ስንፍናን አይወድምና ልጆቻችንን ታታሪነት ማስተማር አለብን። መጽሐፍትን ማንበብ እንዲወዱ ማድረግ አለብን።

ወገኖቼ፦ ልጆቻን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲማሩ በቤታችን መጽሐፍ ቅዱስን አብረናቸው ማጥናት አለብን፤ ሁልጊዜ ስለ ልጆቻችን መጸለይ አለብን፤ በቤተ ክርስቲያን ፕሮግራሞች ላይ በትጋት እንዲሳተፉ ማድረግ አለብን። እግዚአብሔር እንደሚረዳቸውና የልቀትን መንፈስ እንደሰጣቸው ማስተማር አለብን። በስንፍና ደግሞ ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ትጋትን ማሰነቅ አለብን። እግዚአብሔር ልጆቻችንን ይባርክ!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page