top of page

ለመታሰቢያዬ አድርጉት

የእግዚአብሔር ቃል የጌታን እራት ስንወሰድ ለጌታ መታሰቢያ እንድናደርገው ያስተምረናል። ለመሆኑ የጌታን እራት ስንወስድ የምናስበው ምንድን ነው? አንደኛ በጌታ የተደረገልንን እናስባለን። ይህም ማለት ስለ እኛ ደህንነት የተቆረሰልንን የጌታን ስጋ እና የፈሰሰልንን የጌታን ደም እናስባለን። እንጀራውን ቆርሰን ስንወስድ የስጋው መቆረስ ምሳሌ ነው። ጽዋውንም ቀድተን ስንጠጣ የደሙ መፍሰስ ምሳሌ ነው። ይህ ደግሞ ለተካፈልነው ሕይወት መሰረት ነው። ጌታ ኢየሱስ በቃሉ እንዳለ የጌታን ስጋ የበላ ደሙንም ደግሞ የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። ከርሱ ጋራም ህይወትንና ትንሳኤን ይካፈላል (ዮሐ. 6:54,56)። እኛ ሕይወት ያገኘነው በጌታ ሞት ነው። ሞቱ የኛ ሞት ነው። በደሙም ከሃጢያታችን ታጠብን። በጌታ ሞት ከአብ ጋራ ታረቅን። በስጋው መቆረስ ለኛ ተዘግቶ የነበረው መጋረጃ ተቀዶ ወደ አብ የምንቀርብበት አዲስና ህያው መንገድ ተከፈተልን። ስለዚህም የጌታን እራት ስንወስድ አንዱ የምናስበው የጌታን ሞት ነው።

የጌታን እራት ስንወስድ የምናስበው ሁለተኛው ነገር ይህንን ስርዓት በእምነት ስናደርግ አሁን በሕይወታችን የሚሰራውን ነው። ቃሉ እንደምያስተምረን “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” ይለናል(1ቆሮ. 11:26)። እንጊዲህ ከእንጀራውና ከጽዋው ስንካፈል የጌታን ምት ለመናገር አቅም እናገኛለን። ይህም ማለት ሞቱን፣ በሞቱም ያገኘነውን ሕይወት እንዲሁም በሞቱ የተገለጸው ፍቅር በህይወታችን አዲስ ሆኖ መንፈሳዊ ግለትን ያመጣልናል። ስለዚህም ጌታ ወዶኝ ሞቶልኛል እንላለን፤ ለሌሎችም ይንን አስደናቂ እውነት እንመሰክራለን። እዚህ ላይ በክፍሉ እንደምናነበው የጌታን እራታ ሳይገባቸው (ሳይረዱት ወይንም ህይወታቸውን ሳይመረምሩ) የሚወስዱ ሁሉ ሊደክሙ፣ ሊታመሙ ሊያንቀላፉም ይችላሉ (ቁ. 30)። ይህ እንግዲህ የጌታ እራት በአማኙ ውስጥ የሚሰራው ስራ እንዳለ ያሳየናል። ሳይገባቸው የወሰዱ ከደከሙ፤ ተገብቷቸው የሚወስዱ ደግሞ ይበረታሉ። ሳይገባቸው የሚወስዱ ከታመሙ፤ ተገብቷቸው የሚወስዱ ደግሞ ይፈወሳሉ። ሳይገባቸው የሚወስዱ ካንቀላፉ፤ ተገብቷቸው የሚወስዱ ደግሞ የበዛ ሕይወት ይሆንላቸዋል።

የጌታ እራት በሶስተኛ ደረጃ የጌታን ዳግም ምጽአት ያሳስበናል። በቃሉ እንዳየነው እንጀራውን በበላን ጊዜና ጽዋውን በጠጣን ጊዜ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን እንናገራለን። በዚህ ቃል ውስጥ የጌታ መምጣት ተስፋ ተሰጥቶናል። ጌታችን ወደ መስቀል ከመሄዱ በፊት “ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ብሎናል (ዮሐ. 14:1-3)። ጌታ ዳግመኛ ይመጣል። መጥቶም ወደ ራሱ ይወስደናል። ቃሉ የታመነና እውነት ነው። እንዲሁም ደግሞ ጌታ ይህንን ስርአት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲያደርግ እንዲህ አለ፡ “ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም” (ማቴ. 26:29)። እንግዲህ የጌታን እራት ስንወስድ ሌላው የምናስበው ከጌታ ጋር በእግዚአብሔር መንግስት እራት እንደምንካፈል ነው። ይህ የተባረከ ተስፋችን ነው። ጌታ ይመጣል። አዎን ማራናታ!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page