top of page

መንፈስ ቅዱስ አሳሳቢ (አስታዋሽ) መንፈስ

“አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ... እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዮሐ. 14፡26)።

መንፈስ ቅዱስ ግሩም አስተማሪ ነው። መንፈስ ቅዱስ በአብ ውስጥ ያለውን ስለሚያውቅ የጠለቀውን የቃሉን ፍቺ ያበራልናል። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ቅዱስ የቃሉ ደራሲ ስለሆነ በቃሉ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ኃሳብ ለቅዱሳን ያሳውቃል። ስለዚህም ወደ መንፈስ ቅዱስ የበለጠ ስንቀርብ እግዚአብሔርን የበለጠ እያወቅን እንሄዳለን። መንፈስ ቅዱስ የቃሉ አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ቃሉንም የሚያሳስብ መንፈስ ነው።

መንፈስ ቅዱስ አሳሳቢ(አስታዋሽ) መንፈስ ነው። በውስጣችን ያለውን ቃል በሚያስፈልገን ጊዜ ወደ ልባችን የሚያመጣው መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለዚህም ቃሉ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ያስተማረንን ሁሉ “ያሳስባችኋል” (የሐ. 14:26) ይለናል። በዚህ ቃል ዋስትና ወንጌላዊያኑ ኢየሱስ ያስተማረውን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አስታውሰው ጻፉልን። እንዲሁም በአገልግሎታቸው ሁሉ መንፈስ ቅዱስ የጌታን ቃል ያስታውሳቸው ነበር። ለምሳሌ ሐዋሪያው ጴጥሮስ በመቶ አለቃ ቆርኖሊዮስ ቤት ወንጌልን ከሰበከ በኋላ በአሕዛብ ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱን መንፈስ ቅዱስ ቃሉን ወደ ልቡ በማምጣት አረጋገጠለት። ሐዋሪያው ስለዚህ ሁኔታ “ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ” በማለት እንዴት መንፈስ ቅዱስ ለነበረበት ሁኔታ ቃሉን እንዳስታወሰው ጽፏል (ሐዋ. 11:16)። እንዲሁም ጌታ ስለሞቱና ስለ ትንሳኤው የተናገረውን እንዲሁም በትንቢት ስለ እርሱ የተጻፈውን ለሐዋሪያቱ ያሳታወሳቸውና ያበራላቸው መንፈስ ቅዱስ ነው (ዮሐ. 2:22፤ 12:16)።

ዛሬም ከቃሉ የተማርነውን እውነት የሚያስታውሰን መንፈስ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በሙላት እንዲኖርብን ያዘናል (ቆላ. 3:16)። የእግዚአብሔር ቃል በሙላት በውስጣችን ካለ በሚያስፈልገን ግዜ መንፈስ ቅዱስ ለጊዜው የሚሆነውን ቃል ያሳስበናል (ያስታውሰናል)። በቃሉ የተሞላን ሰው መንፈስ ቅዱስ በማንኛው ሁኔታ የሚያሰላስለውን ቃል ያሳስበዋል። ቃሉን በቀንና በሌሊት የሚያስብ ሰው “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” (መዝ. 1:3)። እንዲህ አይነቱ ሰው በማንኛው ሁኔታ ውስጥ አይሰጋም፤ ደስታው ሙሉ ነው፤ ሁልጊዜም ፍሪያማ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እንዲህ ያለው ሰው በቃሉ ውስጥ ስለሚኖር ነው። ለለዚህ እግዚአብሔር ለኢያሱ የሰጠው ዋና ምክር “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም” (ኢያ. 1:8) የሚል ነው።

ወገኖቼ፦ በእግዚአብሔር ቃል ውስጣችን ከተሞላ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን ያስተውሰናል። ቃሉበሙላትከሌለበንግንመንፈስቅድስየሚያስታውሰንነገርአይኖረውም። ምክንያያቱም ለማስታወስ የሚንችለው በውስጣችን ያለውን ነው። ቅዱሳን ቃሉ በሙላት ይኑርብን። በቃሉ እንጽናናለን፣ ጠላቶቻችንን ድል እንነሳለን፣ ጸንተን እንቆማለን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page