top of page

መንፈስ ቅዱስ እንኳን ደህና መጣህ!

ወንጌላዊ ቤን ሂን ከጻፋቸው መጽሃፍት መካከል “Welcome Holy Spirit” – “መንፈስ ቅዱስ እንኳን ደህና መጣህ” እና “GoodmorningHolySpirit”–“መንፈስ ቅዱስ እንደምን አደርክ” የሚሉት ይገኙበታል። በነዚህ መጽሐፍቱ ወንጌላዊው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን የእለት ተለት ቅርርብ አንጸባርቋል። መንፈስ ቅዱስ ስብእና (personality) ያለው አምላክ ነው። ከአብና ከወልድ ጋር ትክክል የሆነ ከስላሴ አንዱ ነው። መንፈስ ቅዱስ የኃይል መንፈስ እንጂ ኃይል ብቻ አይደለም። ጌታ ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን “እርሱ” እየለ በሰው መደብ ነው የገለጸው። (ዮሐ 14፡ 16-17፣25፣ 15፡26፣ 16፡ 5-15) መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ ነው። በፍጥረት ውስጥ ከአብና ከወልድ ጋር ተካፍሏል። (ዘፍ 1፡2) ልክ ዶሮ እንቁላሎቿን እንደምትታቀፍ የእግዚአብሔር መንፈስም በፍጥረት ጌዜ ባዶ የነበረውን ሊሞላ፣ ጭለማውን ሊገልጥ፣ ቅርጽ አልባ የነበረውን ቅርጽ ሊሰጥ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር። ይህም ስራው ዛሬም የቀጠለ ነው። ዛሬም መንፈስ ቅዱስ ይፈጥራል፣ ጭለማውን ይገልጣል፣ ባዶውን ይሞላል፣ ቅርጽ የሌለውን ቅርጽ ይሰጣል። እዮብ “የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጥሮኛል፤ ሁሉን የሚችለውም አምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጥቶኛል” (እዮብ 33፡4) እንዳለ የተፈጠርነው በእግዚአብሔር መንፈስ ነው።

መንፈስ ቅዱስ ስሜት አለው። በኤፌሶን 4፡30 ላይ “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” በማለት ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ይመክረናል። ክፍሉን ስንመለክተው የሚያንጽና የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከውስጣችን እንዳይወጣ ነው የሚያስተምረው። መራርነትን፣ ቁጣን፣ ንዴትን፣ ጭቅጭቅን፣ ስድብን፣ ክፋትን እንድናስወግድ ይነግረናል። ይቅር እንድንባባል ያሳስበናል። ይህ በማይሆንበት ቢዜ -- ይቅር መባባል ሳንችል ስንቀር፣ ረብ የለሽ ቃል ከኛ ሲወጣ፣ የስጋ ፍሬ ሲሰለጥንብን -- የታተምንበት መንፈስ ቅድስ (በውስጣችን ያለው) ያዝናል። ማዘን የስብእና ምልክት (የስሜት ምልክት) ነው። መንፈስ ቅዱስ የሚያዝነው ስለሚወደን ነው። ምክንያቱም ማዘን የፍቅር ቋንቋ ነውና። ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው የምትወዱት ሰው ቢበድላችሁ ስሜታችሁ በዋናነት የሚገለጠው በማዘን ነው። መንፈስ ቅዱስ ስለሚወደን ስንበድለው ያዝናል።

መንፈስ ቅዱስ በአንድ ጌዜ ሁሉም ቦታ የሚገኝ ነው (He is Omnipresent) ከኛ ጋር ነው፣ በኛም ውስጥ ነው። አሁን በዚህ ሰአት በአለም ሁሉ አለ። መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ቻይ ነው (He is almighty) ጌታ የምድር አገልግሎቱን ያካሄደው በምንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቀብቶ ነበር። ጌታ ኢየሱስም ይህንኑ እውነት “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” (ሉቃ 4፡17) በማለት አረጋግጦልናል። ወገኖቼ፦ እኛም ለወንጌል ምስክሮች መሆን የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። መንፈስ ቅዱስ የሃይል፣ የፍቅርና ራስን የመግዛት መንፈስ ነው። መንፈስ ቅዱስን ሁልጌዜ “መንፈስ ቅዱስ ሆይ እንኳን ወደ ሕይወቴ፣ ወደ ቤቴ፣ ወደ አገልግሎቴ... ደህና መጣህ” እያልን እውቅና እየሰጠን እንቀበለው። አሜን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page