እግዚአብሔር እረኛዬ ነው።
መዝሙር 23 ዳዊት ከዘመራቸው ዝማሬዎች መካከል በጣም ታዎቂውና ተወዳጁ ነው። በዘመናት መካከል ይህ መዝሙር ብዙዎችን አበርትቷል፣ አጽናንቷል፣ እንዲሁም ተስፋ ሰጥቷል። በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ይህንን መዝሙር የጻፈው ንጉስ ዳዊት እራሱ እረኛ እንደ ነበረ ሁሉ የእግዚአብሔርንም መልካም እረኝነት በዚህ መዝሙር ውስጥ ውበት ባለው ቋንቋና ከሳች ምሳሌ ገልጾልናል። መዝሙሩ በእግዚአብሔር ላይ ያለ መታመንን በማጉላት መጋቦቱን፣ ምሪቱን፣ ጥበቃውን፣ አብሮነቱን፣ እና ዘላለማዊ እቅዱን ያሳያል።
የመዝሙሩ የመጀመሪያ አንጓ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው” ይላል። በነዚህ ሶስት ቃላት እጅግ በጣም የታመቀ እውነታ ተቀምጧል። በመጀመሪያ እግዚአብሔር የህዝቡ “እረኛ” ነው የሚለውን ሃሳብ እናገኛለን። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እግዚአብሔር የሕዝቡ እረኛ እንደሆነ በስፋት ተዳሶ እንመለከታለን። ለምሳሌ በኢሳያስ 40:11 ላይ እግዚአብሔር “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል” ተብሎ ተገልጿል። እዚህ ስፍራ የምናየው ምስል እግዚአብሔር አምላክ ለሕዝቡ የሚራራ፣ ትጉ፣ አፍቃሪ እረኛ እንደሆነ ነው። መንጋውን በትኖ አይተዋቸውም፤ ይልቁንም በመልካም ስፍራ ያሰማራቸዋል። ሕጻናቱን ይሸከማል፣ የሚያጠቡትን አያስቸኩልም። በሕዝቅኤልም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡን ቸል ያሉትን እረኞች በመውቀስ እርሱ ራሱ ለሕዝቡ እረኛ እንደሆነ ይናገራል። በተለይም ስለ እረኝነቱ ሲናገር “እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ...የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ” ይላል (ሕዝ. 34፡15-16)። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበጎች “መልካም እረኛ” (ዮሐ. 10፡ 11) እንደሆነ ተገልጿል። ጌታችን ስለ በጎቹ ነፍሱን የሰጠ መልካም እረኛ ነው (ቁ. 11፣ 15)። ጌታ በፍቅር የሚመራ፣ እያንዳዱን በግ የሚያውቅ መልካም እረኛ ስለሆነ በጎቹ ድምጹን ያውቃሉ፣ ደግሞም ይከተሉታል (ቁ. 27)። የእብራውያን ጸሐፊም የጌታችንን ዘላለማዊ እረኝነት ሲገልጽ “በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ” (ዕብ. 13:20) ይለዋል። የጌታችን እረኝነት ለዘላልም በደሙ ቃል ኪዳን የጸና ነው። ስለዚህም ከእጁ ማንም ሊነጥቀን አይችልም። ሐዋሪያው ጴጥሮስ ደግም የነፍሳችን “እረኛና ጠባቂ” እንዲሁም “የእረኞች አለቃ” (1ጴጥ. 2:25፣ 5:4) ይለዋል። እንዲሁም በመጨረሻ በጉ እረኛችን እንዲሚሆን ሐዋሪያው ዮሐንስ ሲጽፍልን “በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል” (ራዕ. 7:17) ብሏል። እግዚአብሔር ለዘላለምም የሕዝቡ እረኛ ነው።
ሁለተኛው በዚህ መዝሙር መግቢያ ላይ የምናገኘው ሃሳብ እግዚአብሔር በግል (ለእያንዳንዳቸን) እረኛ እንደሆነ ነው። ዳዊት የሚዘምረው የጅምላ መዝሙር ሳይሆን ከግል ልምምድ የወጣ፣ እግዚአብሔርን በማወቅ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን እረኝነት ነው። ስለዚህም “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው” አለ። “እረኛዬ” የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን አጠቃላይ እረኝነት ብቻ የሚናገር ሳይሆን እግዚአብሔር የዳዊት እረኛ እንደሆነ ነው። ዳዊት የእግዚአብሔርን እረኝነት በሕይወቱ ተለማምዷል። እረኝነቱን በጦር ሰልፍ ያውቀዋል፣ እረኝነቱን በምድረ በዳ ያውቀዋል፣ እረኝነቱን በስደት ያውቀዋል፣ እረኝነቱን በብቸኝነት ያውቀዋል። ስለዚህም ዳዊት ይህንን መዝሙር የተቀኘው የአምላኩን እረኝነት በሕይወቱ ቀምሶ ነው። እኛስ ዛሬ እረኝነቱን በግል እየተለማመድን ነው ወይ? (ይቀጥላል)