top of page

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- የሚያሳጣኝም የለም።

ባለፈው ሳምንት እንዳየነው መዝሙር 23 እግዚአብሔር የሕዝቡ እረኛ እንደሆነ ያስተምረናል። ከዚህም ተነስተን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር እረኝነት የሚያስተምረንን ሃሳቦች በጥቂቱ አይተናል። በተጨማሪም ዳዊት የራሱን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን የግል ልምምድ መሰረት አድርጎ እግዚአብሔር ለእርሱ በግሉ እረኛው እደሆነ በመረዳትይህንን መዝሙር እንደዘመረተመልክተናል። ዛሬደግም “የሚያሳጣኝምየለም” የሚለውን ሃሳብ እናያለን።

ዳዊት እግዚአብሔር እረኛው ስለሆነ የሚያሳጣው ነገር እንደሌለ ያውጃል። “የሚያሳጣኝም የለም” በሚለው ክፍል ውስጥ የምናገኘው አንዱ ሃሳብ በእግዚአብሔር ላይ መታመን ነው። እግዚአብሔር ለሕይወትና ለኑሮ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል። እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሰው የሚያስገልገውን ሁሉ ካዘጋጀ በኋላ ነው ሰውን የፈጠረው። ሰው ፍጥረትን ሁሉ እንዲገዛናእንዲስተዳደር እግዚአብሔር በፍጥረቱ ሙላት ውስጥ አስገባው። (ዘፍ. 1፡ 28-30) አሁንም ፍጥረትን ሁሉ የሚመግበው እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ ጉዳይ ዳዊት ሲዘምር “የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” ይላል (መዝ. 145፡ 15-16)። እግዚአብሔር የፍጥረቱ ሁሉ መጋቢ ከሆነ ለልጆቹ ደግሞ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚሰጥ ጥርጥር የሌለው ጉዳይ ነው። ጌታችን ባስተማረው የተራራው ስብከት “እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ... ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና” በማለት እግዚአብሔር የሚያሳጣን እንደሌለ አስተምሮናል (ማቴ. 6፡ 31-32)። የኛ ፋንታ የእግዚአብሔርን መንግስትና ጽድቅ መፈለግ ነው። እግዚአብሔር የሚስፈልገንን ሁሉ ይጨምርልናል። (ቁ. 33) ንጉስ ዳዊትም “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” በማለት እግዚአብሔርን የሚፈልግ ፈጽሞ እንደማይጎድል ዘምሯል። ዳዊት ይህንን የዘመረው የሕይወት ዘመን ተመክሮውን ተመልክቶ ነው። በጉልምስና እና በእርጅና መካከል በትንሹ አርባ አመት አለ። በዚህ ረጅም የህይወት ተመክሮው ዳዊት የሚመስክረው ነገር በእግዚአብሔር ላይ ተደግፎ የሚያፍር ማንም እንደሌለ ነው።

ሁለተኛው “የሚያሳጣኝም የለም” የሚለው ሃረግ የሚያመለክተው በተሰጠን ነገር መርካትና ማረፍ እንዳለብን ነው። ይህ ክፍል በኪንግ ጄምስ የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “I shall not want” ተብሏል። ሃሳቡ እግዚአብሔር እረኛችን ከሆነ ሙሉ በሙሉ በእርሱ እንደምንረካና እንደምናርፍ የሚያሳይ ነው። ሰው በቁሳዊ ነገር ፍጹም እርካታ ሊያገኝ አይችልም። እንዲሁም በቁሳዊ ነገር ለመርካት አይቻልም ምክንያቱም ቁሳዊ ነገር ከፊታችን እንደ ሚሸሽ ኢላማ ሁልጊዜ ደረስኩበት ስንል እልፍ የሚል በመሆኑ ነው። እግዚአብሔር ግን ፍጹም የሚያሳርፍ አምላክ ነውና እግዚአብሔር እረኛው የሆነ ሰው የተሟላ፣ የረካና ያረፈ ሰው ነው። ሌላ የሚያረካ ምንጭ አይፈልግም። ነገር ግን የተቀበለው መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ “ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ” ይሆንለታል (ዮሐ. 4:14)። እግዚአብሔር በእርሱ የምትደገፈውን ነፍስ ፈጽሞ በሰላሙ ይጠብቃታል (ኢሳ. 26:3)። እግዚአብሔር ሸክማቸው የከበደውን ሁሉ የሚያሳርፍ እውነተኛ እረፍትና እርካታን የሚሰጥ አምላክ ነው (ማቴ. 11:28፣ መዝ. 46:10፣ 1ጴጥ. 5፡7)። ወገኖቼ፦ ከእግዚአብሔር ውጪ ሙላትና እርካታ የለም። እርሱ እረኛችን ከሆነ የሚያሳጣን የለም።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page