top of page

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል።

የእግዚአብሔር እረኝነት ከሚገለጥበት መንገድ አንዱ የእርሱመጋቦት ነው። እግዚአብሔር እረኛችን ስለሆነ ይመግበናል። በመዝሙር 23 ዳዊት የእግዚአብሔርን መጋቢነት ሲገልጽ እግዚአብሔር በለመለመ መስክ እንደሚያሳድረውና በእረፍትም ውሃ ዘንድ እንደሚመራው በመተማመን ያውጃል። ይህ መተማመን የመጣው የእግዚአብሔርን መልካም እረኝነት ተለማምዶ ከመወቅ ነው።

በጎች ለመኖር ምግብና ውሃ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህም መልካም የሆነ እረኛ የሚያደርገው አንዱ ነገር በጎቹ እንዳይራቡና እንዳይጠሙ ግጦሽ ባለበት የለመለመ መስክ ያሰማራቸዋል። እንዲሁም በልተው ደግሞ የሚረኩበት ውሃ እንዲያገኙ ተረጋግተው ሊጠጡት ወደ ሚችሉት የእረፍት ውሃ ይመራቸዋል። ጌታ ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን እርሱ እውነተኛ “የበጎች በር” እንደሆነ ተናግሯል (ዮሐ. 10:7)። ከሰጠን ተስፋዋች መካከልም “በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል” የሚል ይገኝበታል (ቁ. 9)። እንግዲህ ወደ ጌታ ስንመጣ ቃሉ “በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል” እንደሚል በዋናነት ድነትን እናገኛለን። ደግሞም ቃሉ “ይገባል ይወጣል” ስለሚል በርሱ አስተማማኝጥበቃን እናገኛለን። በመጨረሻም “መሰማርያምያገኛል”እንደሚል በጌታለኑሮ የሚያስፈልገንን እናገኛለን። ጌታ ያድናል፣ ይጠብቃል ደግሞም በመልካም ያሰማራል።

ጌታ የሚያሰማራው በለመለመ መስክ እና በእረፍት ውሃ ዘንድ ነው። ይህ የሚያሳየን በጌታ ስንሆን መጋቦቱ እንዳማይጓደልብን ብቻ ሳይሆን በመጋቦቱ ውስጥ ያለውንም እርካታ ጭምር ነው። መሰማሪያን ማግኘት አንድ ነገር ሲሆን “የለመለመ” መሰማሪያን መግኘት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ልምላሜ ያለበት መሰማሪያ እርካታ ያለበት መሰማርያ ነው። ጌታ በሚሰጠን ነገር ውስጥ ፍላጎታችን ብቻ የሚሟላበት ሳይሆን እረፍትና እርካታ ያለበት ነው። ባለን ነገር ደስ ይለናል። የማጣትና የመጉደል ነገር አይሰማንም።

ከዚህ አንጻር ዛሬ ጌታ አሰማርቶን ባለበት ስፍራ እጅግ በምስጋና እንድሆን ያስፈልገናል። እረኛችን ለኛ የሚስፈልገውን ያውቃል። እርሱ የሰጠን ሕይወት፣ እርሱ የሰጠን ስፍራ፣ እርሱ የሰጠን ትዳር፣ እርሱ የሰጠን ስራ፣ እርሱ የሰጠን ቤት፣ እርሱ የሰጠን ልጆች... ወዘተ መልካም ነው። የለመለመ መሰማሪያ ነው። እረኛችን ባሰማራን ስፍራ በምስጋና እና በደስታ እንሁን። አሁን በአለም ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር አለመርካት ነው። ሰዎች ብዙ ነገር እያላቸው አይረኩም። በሞላ ቤት ውስጥ ብቸኝነት ያጠቃቸዋል። አንዳድ ጊዜ ደግሞ ብዙ እያላቸው ጨምረው ብዙ ማከማቸት ይፈልጋሉ። የሰው የፍላጎት ቋት አይሞላም -- የገንዘብ ከርሱ አይጠግብም፣ የስልጣን ጥማቱ አይረካም፣ ያዝና መሻቱ አይቆምም። ለእኛ ግን እንዲህ አይደለም። ጳውሎስ “የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁ” (ፊል. 4:11) ብሎ እንዳለ ለኛ አሁን የተሰማራንበት ስፍራ መልካም ነው፤ በቂ ነው፤ የለመለመ ነው። አዳንድ ጊዜ ደግሞ የሰው ፈተና የኋልዮሽ መመልከት ነው። እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ እንዲህ እሆን ነበር እያለ ያለፈው በመሰለው እድል እየተቆጨ ዛሬውን ያበላሻል፤ ነገውንም ያጨፈግጋል። ለኛ ግን እንዲህ አይደለም። ለኛ ዘማሪው “ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፥ ርስቴም ተዋበችልኝ” (መዝ. 16:6) እንዳለ አምላካችን የሰጠን አሁን ያለንበት ኑሮ የተዋበ ነው። እርሱ ለኛ የሚያስባትን ሃስብ ያውቃል -- ፍጻሜና ተስፋ ያለበት የሰላም ኃሳብ ሰጥቶናል (ኤር. 29:11)። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page