top of page

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም።

በዚህ ክፍል ዳዊት ሞት እንደማያስፈራው ይዘምራል። በመሰረቱ ሞት በክርስቶስ የመስቀል ስራ አምኖ ከእግዚአብሔር ጋር ላልታረቀ ሰው አስፈሪ ነው። በጌታ ያልሆነ ሰው ምንም ጀግና ቢሆን ከሞት ጋር ሲፋጠጥ ይፈራል። ለዚህ ነው አጋግ የተባለው የአማሌቅ ንጉስ ሳሙኤል ፊት ሲቀርብ “በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን?” ያለው (1 ሳሙ. 15:32)። በክርስቶስ የሆንን ቅዱሳን ግን ከሞት ፍርሃት ነጻ ወጥተናል።

ሞት አስፈሪ የማይሆነው የመውጊያ ኃይሉ ሲወሰድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን የሞት መውጊያ ኃጢያት ነው። ሞት በኃጢያት አማካኝነት ይነድፍና ይገድላል። በኃጢያት የሚመጣው ሞት ደግሞ መንፈሳዊ ሞትን፣ ስጋዊ ሞትንና የዘላለም ሞትን የሚጠቀልል ነው። ሰው በኃጢያት ሲወጋ በመጀመሪያ የደረሰበት የመንፈስ ሞት ነው። ይህም ከእግዚአብሔር ጋር መለየት ሲሆን የተገለጸውም በውስጥ ማንነታችን (በመንፈሳችን) መሞት ነው። ስለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ስለነበርነበት ሁኔታ ሲናገር “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ” የሚለን (ኤፌ. 2:1)። ይህም ሞት ከእግዚአብሔር ፍቃድ ይልቅ በዲያቢሎስ ፍቃድና በስጋችን ፍቃድ በመኖር የሚገለጥ ነው። አዳሞ በኃጢያት በተነደፈ እለት መንፈሳዊ ሞትን ሞተ። ያንንም ተከትሎ በስጋ መሞት በእርሱና በዘሩ ገባ። በክርስቶስም ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር ካልታረቀ ደግሞ መጨረሻው የዘላለም ሞት -- ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየት ይሆናል።

ዳዊት በመዝሙር 23 ላይ “በሞት መካከል እንኳ ቢሄድ” ሳይሆን የሚለው “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ” ነው የሚለው (ቁ. 4)። “ጥላ” አካል አይደለም። በእርግጥ “ጥላ” መኖሩ “አካል” እንዳለ ይገልጻል። ነገር ግን የሞት ኃይል ወደ እኛ ሊቀርብ አይችልምና “ጥላው” አያስፈራንም። ስለዚህ ዳዊት በትንቢታዊ መረዳት በክስቶስ ላሉት ሞት ኃይሉ ተወስዶ ጥላው ብቻ የቀረ አስፈሪነቱ የተሻረ እንደሆነ ዘመረ። መዝሙሩ በመጀመሪያ የሚያስተምረን አሁን በኛ ላይ ሞት ኃይል ያለው ሳይሆን ጥላው ብቻ የቀረ ኃይሉ የተገፈፈ እንደሆነ ነው። ሞት በኛ ላይ ሊሰለጥን አይችልም። “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” (1 ቆሮ. 15:55) ተብሎ እንደተጻፈ ሞት መውጊያው ተወስዶ ያለ መንደፊያ የቀረ “ጥላ” ብቻ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ በሞት ላይ ስልጣን የነበረውን ዳቢሎስን ሽሮታል (ዕብ. 2:14-15)። ስለዚህም ለኛ ሞት ወደ ክርስቶስ የምንሻገርበት ነው እንጂ የሚያስፈራን አይደለም። ስለዚህ ዳዊት “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ቢሄድ” አልፈራም ይላል። ሌላው የምንገነዘበው ነጥብ ዳዊት “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ” ክፉን አልፈራም ለማለት ያስደፈረው በሞት ላይ ስልጣን ያለው አረኛ ከርሱ ጋር በመሆኑ ነው። ስለዚህም “አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም” ይላል። እግዚአብሔር ከኛ ጋር ስለሆነ የሞት ኃይል አያስፈራንም። ከኛ ጋር ያለው አምላካችን የሞትን ኃይል የሻረ፣ ሞት ሊይዘው ያልቻለ፣ የሞትን ኃይል አጥፍቶ በኃይል የተነሳ ስለሆነ ክፉን አንፈራም።

ወገኖቼ፦ ዳዊት ከብዙ ዘመናት በፊት አሻግሮ አይቶ እንደዘመረው ሞትን የማንፈራው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛ ሞት እኛን ሊወጋ የሚችልበት የኃጢያት መውጊያው ስለተወሰደ ሞት በኛ ላይ አሁን ስልጣን የለውም። ጌታችን ሰው ሆኖ በመስቀል በመዋል በሞት ላይ ስለጣን የነበረውን ዳያቢሎስን ሽሮታል። ሁለተኛ ደግሞ ይህ ዲያቢሎስን እናመሳሪያውንሞትንድልየነሳውጌታከኛጋርነው።ስለዚህእንደንጉስዳዊት“በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም” እያልን እንጓደዳለን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page