top of page

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።

ሰሞኑን በተከታታይ እያየን እንዳለነው እግዚአብሔር እረኛችን ነው -- ይመግበናል፤ እግዚአብሔር እረኛችን ነው -- ይመራናል፤ እንዲሁም ከኛጋርያለውእግዚአብሔርየሞትን ኃይል ስለሻረው በሞት ጥላ መካከል ብናልፍ እንኳ ክፉን አንፈራም። ዛሬ ደግሞ እግዚአብሔር እረኛችን ጠባቂያችን እንደሆነ እንመለከታለን። የእግዚአብሔር እረኝነት ከሚገለጥበት አስደናቂ መንገድ አንዱ ጥበቃው ነው።

እውነተኛ እረኛ ለበጎቹ እራሱን ያኖራል። ጌታ ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል” (ዮሐ. 10:11-12) ብሏል። የእውነተኛ እረኛ ባህሪ በጎቹን ነፍሱን እስከ መስጠት ድረስ መውደዱ ነው። ስሊዚህ ጌታ ነፍሴን ስለ በጎቼ አኖራለሁ አለ። እውነተኛ እረኛ ስለበጎቹ ከጠላት ጋር ይገጥማል። ጠላት ሲነጥቃቸው ሲመጣ ተከትሎ ያስጥላቸዋል። ዳዊት ይህ የገባው እረኛ ስለሆነ አንበሳና ድብ መጥቶ በጎቹን ሲነጥቅ ተከታትሎ ይመታዋል፤ በጎቹንም የጠላቱን ጉሮሮ አንቆ ከአፉ ያስጥላቸዋል (1 ሳሙ. 17፡ 34- 35)። እረኛችን ብርቱና ጽኑ ነው። አስተማማኝ ነው። ማንም ከእጁ ሊነጥቀን የሚችል የለም። ጌታችን ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” (ዮሐ. 6:37) በማለት አስተማማኝ ጥበቃውን አረጋግጦልናል።

ዳዊት እርሱ ለበጎቹ ትጉ እረኛ እንደሆነ እንዲሁ እግዚአብሔርም እርሱን የሚጠብቅ ትጉ እረኛ መሆኑን ተረድቶ ይዘምራል። ስለዚህም ዳዊት በእረኛው በትርና ምርኩዝ ይጽናናል። በትር እረኛው ጠላትን የሚመታበት ነው። በበትር ኃይል ይገለጣል። ሊያጠቃ፣ ሊነጥቅና ሊያጠፋ ጠላት ሲመጣ እረኛው አስተማማኝ በትሩን አንስቶ ጠላትን ይመታዋል። ቁም ነገሩ ጠላት አለመምጣቱ አይደለም። ጠላት ሊመጣ ይችላል። ጠላት ሊከብብ ይችላል። ነገር ግን “ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንዲነድድ ነደዱ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው” (መዝ. 118:12) እንዳለ ዘማሪው ጠላት ቢከብብም እንኳ በአምላካችን የስሙ ኃይል ይቃጠላል፣ ይነዳል፣ ይበተናል። የጌታ ስም ጠላት የሚመታበት ብርቱ “በትር” ነው። ስለዚህ ከኛ ጋር ያለው ብርቱ ስለሆነ በጥበቃው እንታመናለን።

ዳዊት በእረኛው በትር ብቻ ሳይሆን በምርኩዙም ይታመናል። ምርኩዙ ከመስመር ስንወጣ የምንመለስበት፣ ስርዓት የምንይዝበት ነው። ቃሉ “እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል” (ዕብ. 12:10) እንደሚል አምላካችን እንደ መልካም አባት የሚቀጣ ነው። ሲቀጣን አላማው ከቅድስናው እንድንካፈል ነው እንጂ ለመጉዳት አይደለም። የእግዚአብሔር ቅጣት ለጊዜው ሊያሳምም ቢችልም አላማው ግን እኛን ለማረቅና ለማቅናት እንጂ ለመስበር አይደለም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ምርኩዝ አይጎዳንም ነገር ግን ያርመናል። መረን እንዳንወጣ ያደርገናል። ስለዚህ በበትሩ ከጠላት፤ በምርኩዙ ደግሞ ከራሳችን እንጠበቃለን።

ወገኖቼ፦ እረኛችን አስተማማኝ ጠባቂ ነው። ቃሉ “እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም” (መዝ. 121:4) እንዲሚል እርሱ ስለማይተኛ እኛ ተኝተን እናድራለን። እረኛችን ለራሳችንም አሳልፎ አይተወንም። ስለሆነምእንደዳዊት“በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ” ያጸናኑኛል እያልን እንዘምራለን። ስሙ የተመሰገነ ይሁን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page