top of page

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- ቸርነትህና ምሕረትህ ይከተሉኛል።

ንጉስ ዳዊት በተደጋጋሚ በዝማሬው ከሚያነሳቸው ሃሳቦች መካከል የእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት ዋንኞቹ ናቸው። በመዝሙር 23 ላይም የእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንደሚከተሉት በእምነት ያውጃል። ዳዊት በእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት ይታመናል። በመዝሙር 6:4 ላይ “አቤቱ ... ስለ ቸርነትህም አድነኝ” እያለ ይጸልያል። በመዝሙር 26:6 ላይ ደግሞ “አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና” በማለት ይማጸናል። በመዝሙር 51:1 ላይ ደግሞ “አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ” በማለት በንስሃ ይቀርባል። እንደዚሁም እግዚአብሔር ከምህረቱ የተነሳ ምድርን እንደሚመግባት በማስተዋል “ቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል” ይላል (መዝ. 66:11)። ከነዚህ ዝማሬዎች የምናስተውለው ቸርነትና ምህረት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ባህሪይ እንደሆኑና ፍጥረቱንም በቸርነቱና በምህረቱ እንደሚያስብ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ብዙ ጊዜ ቸርነት (lovingkindness) የሚለው ቃል ከቃል- ኪዳን ጋር በተያያዘ መልኩ በኪዳን የሆነን በጎነት ለመግለጽ ውሏል። ከዚህ አንጻር ቃሉ ታማኝነትን የሚገልጽ ነው። ከእግዚአብሔር አንጻር ቸርነት ከፍቅሩ የተነሳ የሚያደርገውን ደግነት የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር በባህሪው ቸር ነው። እግዚአብሔር የወደዳቸውን ሁሉ ከቸርንነቱ ያጠግባቸዋል። እግዚአብሔር ከችርነቱ የተነሳ ሕዝቡን ያስባል (መዝ. 25:7)፤ ሕዝቡን ይጠብቃል (መዝ. 25:7)፤ አመታትን ያቀዳጃል (እድሜን ይሰጣል) (መዝ. 65:11)፤ ድሆችን ያስባል (መዝ. 68:10)፤ ስርዓትን ያስተምራል (መዝ. 119:68) እንዲሁም በሕይወት ያኖራል (መዝ. 119:77)። ባጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ቸርነት እግዚአብሔር ለህዝቡ ያለውን በጎነት የሚገልጽ ነው።

የእግዚአብሔር ምህረት (mercy) ደግሞ ይቅር ባይነቱን የሚገልጽ ነው። እግዚአብሔር የምህረት አምላክ ነው። የእግዚአብሔር ምህረት በህይወት ታኖራለችና ዳዊት “ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል” በማለት ይቀኛል (መዝ. 63:3)። እግዚአብሔር ፍጹም ቅዱስ አምላክ ስለሆነ በፊቱ መቆም የምንችለው ከምህረቱ ብዛት ያተነሳ ነው (መዝ. 5:7)። እግዚአብሔር ሲገለጽ ሁልጊዜ መኃሪ መሆኑ ይታሰባል። በዘጸአት 20:6 ላይ እግዚአብሔር ማንነቱን ሲገልጽ “ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ” በማለት ምሕረት ባሕሪው እንደሆነ ተናግሯል።

የእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት የማይነጣጠሉና የማይለወጡ የዘላለም ባህሪያቱ ናቸው። በብሉይ ኪዳይ በሕዝቡ ላይ እግዚአብሔር ምህረቱንና ቸርነቱን ገልጿል። በአዲስ ኪዳንም በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አስደናቂ ምህረትና ቸርነት ተገልጧል። እግዚአብሔር በምህረቱ ባለጠጋ ስለሆነ በበደላችን ሙታን በሆንን ጊዜ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን (ኤፌ. 2:5)። እንዲሁም በኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ከክርስቶስ ጋር አስነሳን፤ ከእርሱም ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን።

ወገኖቼ፦ መዝሙረኛው ዳዊት የእግዚአብሔር ቸርነትና ምህረት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንደሚከተሉት እንደዘመረ ሁሉ እኛም የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጫ የሆኑት ቸርነቱና ምህረቱ በየእለቱ ያኖሩናል። ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር በእምነት ስንቀርብ ቸርነቱንና ምህረቱን ያበዛልናል። በያንዳንዱ ቀንም በቸርነቱና በምህረቱ እንታመናለን። የእግዚአብሔር ስም የተባርከ ይሁን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
spotify-badge-button-listen-wh-BG.png
apple-podcasts-logo.jpg
Google-Podcasts-Badge.jpg
RadioPublicc.png
breaker.png
pocketcasts3.png
Anchor-Podcast-Logo.png

 

5850 N. Elston Avenue 

Chicago, Il 60646

10:00 AM TO 12:00 PM SUNDAY

7:00PM TO 9:00PM FRIDAY

  • Facebook Social Icon
  • Twitter Social Icon
  • Google+ Social Icon
  • YouTube Social  Icon
bottom of page